Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በፓኪስታን በህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ላይ በተከሰተ አደጋ 37 ሰዎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፓኪስታን በሁለት የተለያዩ ቦታወች ላይ በተከሰተ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ አደጋ 37 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች መጎዳታቸው ተገለፀ፡፡

የመጀመሪያው አውቶብስ 70 ሰዎችን አሳፍሮ ከኢራን ተነስቶ ፑንጃብ ወደ ተባለችው የፓኪስታን ግዛት እየተጓዘ በነበረበት ወቅት በተከሰተ አደጋ የሰው ህይወት የቀጠፈ ጉዳት ማስተናገዱ ተመላክቷል፡፡

በአደጋው 11 የሚሆኑ ሰዎች ሲሞቱ ከ35 በላይ የሚሆኑት ደግሞ መጎዳታቸው ነው የተገለጸው፡፡

ሁለተኛው አውቶብስ 35 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ በጉድጓድ ውስጥ መግባቱ የተገለፀ ሲሆን በአደጋው ቢያንስ 26 ሰዎች ህይዎታቸው ሲያልፍ ሶስት ሰዎች ደግሞ ተጎድተዋል፡፡

በሁለቱም ቦታዎች ላይ የተከሰቱ የአውቶብስ አደጋዎች ምክንያታቸው በውል አልታወቀም ተብሏል፡፡

ፖሊስ እና የነፍስ አድን ሰራተኞች በአደጋው የተጎዱ ሰዎችን ለማዳን ርብርብ እያደረጉ እንደሚገኙ መገለፁን ቢዝነስ ስታንዳርድ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version