አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የህክምና ስፔሻሊቲ ባለሙያዎችን እጥረት ለመፍታት የሚያስችል ብሔራዊ የስፔሻሊቲ ፕሮግራም በመተግበር ፍትሃዊ የህክምና ባለሙያዎች ተደራሽነት ላይ እየተሰራ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ለጤና ባለሙያዎች የሚሰጠው ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ስልጠና ታካሚዎች ጥራትና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በሚኒስቴሩ የሰው ኃብት ልማትና ማሻሻያ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አሰግድ ሳሙኤል÷ ባለሙያው በየሶስት አመቱ የሚሰጠውን ስልጠና መከታተሉ የህይወት ዘመን ተማሪ እንዲሆን የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
የተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ስልጠና የሚሰጡ ተቋማትን ወደ 255 እንዲሁም ዕውቅና ሰጭ ማዕከላትን ወደ 37 ማሳደግ መቻሉንም አስታውቀዋል።
ባለሙያዎች ስልጠናውን በገፅ ለገፅ እንዲሁም በኦንላይን የሚወስዱበት ስርዓት መኖሩን አንስተው በቀጣይ የኢለርኒንግ ስልጠናን ለማስፋት እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ በሀገሪቱ ያለውን የህክምና ስፔሻሊቲ ባለሙያዎች እጥረት ለመፍታት የሚያስችል ብሔራዊ የስፔሻሊቲ ፕሮግራም በመተግበር ፍትሃዊ የህክምና ባለሙያዎች ተደራሽነት ላይ እየሰራ ነውም ብለዋል።
ፕሮግራሙ በአሁኑ ወቅት ከ1 ሺህ 400 በላይ የጤና ባለሙያዎች በ19 ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በ22 የህክምና ስፔሻሊቲ ስልጠና እየወሰዱ እንደሆነ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የማህፀንና ፅንስ፣ አጠቃላይ ቀዶ ህክምና፣ የአጥንት ቀዶ ህክምና፣ የኒዩሮሎጂ፣ ሳይካትሪ፣ ፎረንሲክ እና የዐይን ህክምና ስፔሻሊቲ እየተሰጡ ካሉት ስልጠናዎች የሚጠቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።