Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ወጣቶች በሰላም ግንባታ የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ወጣቶች በሰላም ግንባታና በልማት ሥራዎች የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣቶችና ስፖርት አማካሪ ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ ጠየቁ፡፡

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ለሰላም ማኅበር ጋር በመተባበር “ወጣቶች በሀገር ሰላምና አካባቢ ጥበቃ ላይ ያላቸው ሚና” በሚል መሪ ሐሳብ ከወጣቶች ጋር ፎረም ማካሄድ ጀምሯል።

አቶ ቀጄላ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት÷ የአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገት ሊረጋገጥ የሚችለው ወጣቱ አምራች ኃይል በሀገሪቱ የልማትና የሰላም ጉዳይ ላይ በንቃት ሲሳተፍ ነው።

ለዚህም መንግሥት በተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ሁሉም ወጣት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ብሎም በአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚያደርገውን የነቃ ተሳትፎ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ለሦስት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው ፎረም ላይ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ከ250 በላይ ወጣቶች ይሳተፋሉ፡፡

Exit mobile version