Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በብራዚል የተከሰተው ሰደድ እሳት በ30 ከተሞች ላይ ተፅዕኖ ማስከተሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በብራዚል ሳኦ ፖሎ ግዛት የተከሰተው ሰደድ እሳት እስከ አሁን ሁለት ሰዎችን ለህልፈት ሲዳርግ በ30 ከተሞች ላይ ደግሞ ተፅዕኖ ማስከተሉ ተገልጿል፡፡

የግዛቱ ባለስልጣናት÷ የተከሰተው ሰደድ እሳት በ30 ከተሞች ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸው፤ ከተሞቹ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደረቅና ሞቃት የሆነ የአየር ጠባይ የታየባቸው መሆኑን አስታውሰዋል።

በአካባቢው የተቀሰቀሰውን ሰደድ እሳት ለመከላከል ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።

የግዛቱ አስተዳደር ከሚነፍሰው ኃይለኛ ነፋስ የተነሳ የሰደድ እሳት በፍጥነት ሊዛመት እንደሚችልና ይህም ዕፅዋትን በስፋት ሊያወድም ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።

በአሁኑ ጊዜ ሰደድ እሳቱ ከ11 ሚሊየን በላይ ነዋሪዎች ወዳሉባት ሳኦ ፖሎ ከተማ እየተዛመተ ስለመሆኑ መንግሥት ያለው ነገር አለመኖሩ ተመላክቷል።

ይሁን እንጂ የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን የአንዳንድ የግዛቱ ከተሞች ሰማይ በጭስ እየተሸፈነ እንደሆነ ዘግበዋል።

መንግሥት በኡሩፔስ ከተማ በሚገኝ አንድ የኢንዱስትሪ ፋብሪካ ውስጥ የሚሰሩ ሁለት ሠራተኞች እሳቱን ለመከላከል ሲሞክሩ ህይወታቸው ማለፉን የገለጸ ሲሆን÷ ተጨማሪ ማብራሪያ አለመስጠቱን ሬውተርስ ዘግቧል፡፡

የዓለማችን ትልቁ የሸንኮራ አገዳ ማቀነባበሪያ የሆነው ራይዘን÷ በሸንኮራ አገዳ ማሳዎች ላይ በተነሳ ቃጠሎ ምክንያት በሰርታኦዚኖ በሚገኝ አንድ ፋብሪካ የኢንዱስትሪ ስራዎች መቋረጣቸውን አስታውቋል።

የሳኦ ፖሎ ግዛት አስተዳደር እሳቱን ለመቆጣተር የድንገተኛ አደጋ ኮሚቴ ያቋቋመ ሲሆን÷ ይህም ወደ 15 የሚጠጉ አውራ ጎዳናዎችን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል መዝጋቱ ተነግሯል።

በብራዚል የሰደድ እሳት ክስተት በአብዛኛው በነሐሴና በመስከረም ወር ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚደርስም ዘገባው አስታውሷል።

Exit mobile version