Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከባድ የስርቆት ወንጀል የፈፀሙ ተከሳሾች እስከ 70 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች ከባድ የስርቆት ወንጀል የፈፀሙ ተከሳሾች በተደራራቢ የክስ መዝገብ እስከ 70 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ተቀጡ።

ሳሙኤል ኃይሉ እና ሳቢር ከድር የተባሉ ተከሳሾች በተለያየ ጊዜ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በተለያዩ ወረዳዎች የግለሰቦችን መኖሪያ ቤት እና የንግድ ቤቶችን በር በመገንጠልና በተመሳሳይ ቁልፍ በመክፈት ላፕቶፕ ኮምፒውተር፣ ቴሌቪዥኖች እና ሌሎች የተለያዩ ዕቃዎችን መሥረቃቸውን ፖሊስ ተገልጿል፡፡

ወንጀል ፈፃሚዎቹን በቁጥጥር ስር በማዋል በተከናወነ ምርመራ የተሰረቁ ንብረቶችን ማስመለሱን የገለጸው ፖሊስ÷ ንብረቶቹን ከወንጀል ፈፃሚዎቹ እየተቀበለች በቤቷ ደብቃ ስታስቀምጥ የነበረች ትዕግስት ስመኝ የተባለች ግለሰብም ተይዛ ምርመራ እንደተጣራባት አስረድቷል፡፡

በሶስቱ ተከሳሾች ላይ በአጠቃላይ ዘጠኝ የክስ መዝገብ መደራጀቱ የተገለጸ ሲሆን÷ ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በአምስቱ መዝገቦች ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።

በዚህም ተከሳሽ ሳሙኤል ኃይሉ በእያንዳንዱ አምስት የክስ መዝገቦች ላይ የተሰጠው ውሳኔ በድምሩ 70 ዓመት እስራት ሲሆን÷ በሁለተኛ ተከሳሽ ሳቢር ከድር ላይ ደግሞ በእያንዳንዱ አምስት የክስ መዝገቦች በድምሩ የ65 ዓመት እስራት ቅጣት መወሰኑን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የተሰረቁ ንብረቶችን በመደበቅ ወንጀል የተከሰሰችው ትዕግስት ስመኝ ከአምስቱ የክስ መዝገቦች በአራቱ በእያንዳንዱ የሶስት አመት እስራት እንድትቀጣ እና ቅጣቱ በገደብ እንዲሆንላት የተደረገ ሲሆን÷ በአንደኛው መዝገብ በተመሳሳይ በሦስት አመት እስራት እንድትቀጣና ቅጣቷን ማረሚያ ቤት ሆና እንድትፈፅም ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ተከሳሾቹ ከተደራጀባቸው ዘጠኝ የክስ መዝገቦች መካከል ውሳኔ ያላገኙ ቀሪ አራት መዝገቦች በሂደት ላይ እንደሚገኙም ነው የተገለጸው፡፡

Exit mobile version