አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለጋራ በጎ ዓላማ በጋራ ስንሰለፍ አቅደን የማናሳካው፣ ጀምረን የማንጨርሰው ተግባር የለም ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷በአንድ ጀንበር 600 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል የተያዘውን ውጥን መላው ሕዝብ በዕለቱ ችግኞችን እንዲተክል የተጠየቀበት እንደነበር አንስተዋል።
ህዝቡም ለጥያቄው ታሪካዊ ምላሹን በተግባር ማሳየቱን ነው የገለጹት፡፡
በየቀኑ ከ40 ሚሊየን ዛፎች በላይ ለሚጨፈጨፉባት ዓለም እኛ ኢትዮጵያዊያን በአንድ ጀምበር ያደረግነው አበርክቶ ፋይዳው እልፍ ነው ሲሉም አውስተዋል፡፡
በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ- ግብር ለተሳተፉ አካላት በሙሉ ለመጭው ትውልድ የማይፋቅ አሻራ በማስቀመጣቸው ምስጋና አቅርበዋል።