የሀገር ውስጥ ዜና

ዛሬ ላይ የሰራነው ገድል ነገ በታሪክ ዘንድ ወርቃማ ካባ ያጎናፅፈናል-አቶ አደም ፋራህ

By Mikias Ayele

August 23, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዛሬ ላይ የሰራነው ገድል ነገ በታሪክ ዘንድ ወርቃማ ካባ ያጎናፅፈናል ሲሉ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

አቶ አደም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷በአንድ ቀን በ600 ሚሊየን ችግኞች  የማልበስ ህልም 615 ነጥብ 7 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል በመጠናቀቁ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ህፃናት፣አረጋውያን፣ሴቶች እና ወጣቶች ስለ ነገዋ  ኢትዮጵያን ብለው አፈር እየማሱ ትውልድን አስበው ደፋ ቀና ሲሉ ማየት ልብን በሃሴት ይሞላል ብለዋል፡፡

በዘር፣በፆታ፣በእድሜ፣በሙያ ሳንከፋፈል ስለ ኢትዮጵያ እና ስለትውልዷ ብለን ዛሬ ላይ የሰራነው ገድል ነገ በታሪክ ዘንድ ወርቃማ ካባ እንደሚያጎናፅፈን ፈፅሞ ጥርጥር የለውም ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የተተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ በማፅደቅ እና የአረንጓዴ አሻራን በእጥፍ በመጨመር የኢትዮጵያ ብልፅግና እና ስልጣኔ በዛፎች እና በተፈጥሯዊ በረከቶች መሀል እንዲዋቀር መንግስት ሃላፊነቱን መወጣቱን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡