አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከተፈጥሮ ጋር እርቅ እንድናወርድ ያስቻለ ነው ሲሉ የብሔራዊ አረንጓዴ አሻራ መርሐ -ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) በመላ ሀገሪቱ እየተካሄደ የሚገኘውን በአንድ ጀምበር 600 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል መርሐ-ግብር አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም ሰፊ የመሬት ክፍል የተራቆተው፣ ብዙ ደኖች የተመነጠሩትና ብዙ ሥርዓተ ምህዳሮች ተናግተው የነበረው በሰዎችና በተፈጥሮ መካከል ተፈጥሮ በነበረው የተዛባ ግንኙነት መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ሰዎች የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር ባደረጉት እንቅስቃሴ መሬት በአስከፊ ሁኔታ መጎዳቱንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ይሁንና ሰዎች ይህን ስናደርግ ተፈጥሮ መከላከል የሚችልበት አቅም ላይኖረው ይችላል ያሉት አስተባባሪው÷ ነገር ግን ቆይቶ ሒሳብ ወደ ማወራረድ ሄዷል ብለዋል፡፡
ከዚህም አንፃር የሰው ልጅ በተፈጥሮ ሃብት ላይ ያደረሰው አግባብነት የሌለው ተፅዕኖ በመጨረሻም ሰውን እራሱን መጉዳት ጀምሯል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ለምሳሌም የአየር ንብረት ለውጥ መምጣት ጋር ተያይዞ ተፅዕኖው ደሃ እና ሃብታም ሳይል በሁሉም የዓለም ሀገራት ላይ አሉታዊ ጫና አሳርፏል ነው ያሉት፡፡
በረሃማነትንም ብንመለከት ከፍተኛ ሙቀትና አነስተኛ ዝናብ እንዲፈጠር ምክንያት ሲሆን÷ ይህም የውሃ እጥረት እና የብዝሃ ሕይወት መመናመን በማስከተል ምርትና ምርታማነትን ይጎዳል፤ ይህም ድህነትንምያመጣል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
እንደ አጠቃላይ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ላይ ባደረሰው ጉዳት የተነሳ ከተፈጥሮ ጋር እንዲሁም ከራሱ ጋር ተጣልቶ ነበር ያሉት አስተባባሪው÷ አሁን ላይ በአረንጓዴ አሻራ ከራሳችንም ከተፈጥሮም የመታረቅ ሥራ ሰርተናል ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር ከ112 ሚሊየን ሄክታር ውስጥ በ54 ሚሊየን ሄክታር ላይ የሥነ ምህዳር መጎሳቆል በጥናት መለየቱን በመግለጽ÷ የመሬት መጎሳቆልንና የደን መጨፍጨፍን ለማስቀረት የችግኝ ተከላ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል፡፡
እየተከናወነ ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ችግኞች ያረፉባቸውን ቦታ መለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።
ችግኞች እየተተከሉ ከሚገኙባቸው ሥፍራዎች በትክክለኛው ቦታ ስለማረፋቸው የሚመጡ መረጃዎችን የማጣራት ሥራም ከባለሞያዎች ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በታምራት ቢሻው