አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ሕብረት ልማት ኤጀንሲ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በትብብር መሥራት እንደሚፈልግ አስታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ከአፍሪካ ሕብረት ልማት ኤጀንሲና የአፍሪካ ልማት አጋርነት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ናርዶስ በቀለ ጋር ባደረጉት ውይይት÷ በኢትዮጵያ እና በኤጀንሲው መካከል በሚኖሩ የሚና እና የትብብር መስኮች ላይ መክረዋል፡፡
በዚሁ ወቅትም የአጀንዳ 2063 መርሐ-ግብሮችን ለማሳካት ኤጀንሲው ከሕብረቱ አባል ሀገራት ጋር በቀጣይነት በትብብር እንደሚሠራ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል፡፡
አምባሳደር ታዬ በበኩላቸው ኤጀንሲው ለአፍሪካ ሀገራት የልማት ሥራዎች እያደረገ ያለውን ያለው ድጋፍ በማድነቅ አጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ልማት ኤጀንሲ (ኦዳ -ኔፓድ) ሕብረቱ በአፍሪካ ቀጣናዊ ውኅደትን ለማሳደግ እና የሕብረቱን አጀንዳ 2063 የልማት ግብ ለማፋጠን የተቋቋመ የኢኮኖሚ ፕሮግራም ነው፡፡