የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ስኬት ተጨማሪ ድጋፎችን እንድናደርግ አነሳስቶናል – የዴንማርክ ኤምባሲ

By Mikias Ayele

August 23, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ስኬት ተጨማሪ ድጋፎችን እንድናደርግ አነሳስቶናል ሲል በኢትዮጵያ የዴንማርክ ኤምባሲ ገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ የዴንማርክ ኤምባሲ የአየር ንብረት እና የንግድ ጉዳዮች አማካሪ ሮዝ ማሬ አርቪድ ላርሰን÷በዛሬው የአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ላይ ተሳትፈዋል።

አማካሪዋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በጠንካራ ሕዝባዊ ተሳትፎ በመተግበር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን መቋቋም የሚያስችሉ ተጨባጭ ውጤቶችን አስመዝግባለች።

ዴንማርክ ከፈረንጆቹ 2018 አንስቶ በኢትዮጵያ የደን ልማት ፕሮጀክት በመተግበር ላይ እንደምትገኝ አስታውሰው÷ በዛሬው መርሐ ግብር ላይ መሳተፋቸው በሀገራቱ መካከል በአረንጓዴ ልማት መስክ ላለው ትብብር ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን በማጠናከር እና የደን ሽፋኗን በማሳደግ ረገድ ለሌሎች ሀገራት ትምህርት የሚሰጥ ተጨባጭ ውጤት ማስገንዘቧን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ አሻራ የሰጠችው ትኩረት  ዴንማርክ ለኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ የምታደርገውን ድጋፍ እንድታጠናክር የሚያደርግ መሆኑንም አስረድተዋል።

በወንደሰን አረጋኸኝ