Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ችግኝ መትከያ ቦታዎች እየተመሙ ነው – መንግስት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ችግኝ መትከያ ቦታዎች አረንጓዴ አሻራቸውን ለማኖር እየተመሙ ነው ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ፡፡

በአንድ ጀምበር 600 ሚሊየን ችግኞች የመትከል መርሐግብርን አስመልክቶ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸው በአንድ ጀምበር 600 ሚሊየን ችግኞች የመትከል መርሐ-ግብር መካሄድ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡

በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ችግኝ መትከያ ቦታዎች አረንጓዴ አሻራቸውን ለማኖር እየተመሙ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ወራት ሲካሄዱ ከነበሩት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በተለየ መልኩ በልዩ ሁኔታ በሳተላይት በተለዩ ቦታዎች የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ እንደሚካሄድ ገልፀዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራመርሐግብር የተመናመነውን የደን ሽፋን ለመመለስ፣ በዓየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ቀጥተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማምጣትና ከተረጂነት ለመላቀቅ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረከተ ተግባር መሆኑንም አነስተዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታትም በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር በአጠቃላይ ከ32 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰዋል፡፡

በዚህም ባለፉት አራት አመታት ብቻ በሀገሪቱ የተተከሉ ችግኞች የኢትዮጵያን የደን ሽፋን በ2012ዓ.ም ከነበረው 17 በመቶ ወደ 23 በመቶ ከፍ ማድረግ ማስቻሉን ገልፀዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

Exit mobile version