አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዛሬ በመላ ሀገሪቱ በአንድ ጀምበር 600 ሚሊየን ችግኞች የመትከል መርሐግብር ይካሄዳል፡፡
ዛሬ ከጠዋቱ 12 ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ ለሚከናወነው በአንድ ጀምበር 600 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል መርሐ ግብር ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ገልፀዋል፡፡
ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ 317 ሺህ 521 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን የገለፀው የግብርና ሚኒስቴር ለተከላ የሚውሉ ችግኞች በቅርብ ሥፍራ ዝግጁ መደረጋቸውን አስታውቋል፡፡
መርሐ ግብሩን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ፥ በአንድ መንፈስ በመላው ኢትዮጵያ ዓሻራችንን እናኑር ፤ አንድ ከሆንን ከዚህም በላይ እንችላለን ሲሉ ጥሪ ማስተላለፋቸው ይታወቃል፡፡
አዋቂዎች ከ20 በላይ፣ ታዳጊዎች ከ10 በላይ በመትከል ለሀገር ያለንን ፍቅር፣ ለትውልድ ያለንን ስጦታ በተገቢው ስፍራ እንግለጥ በማለትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡