የሀገር ውስጥ ዜና

በመቐለ ከተማ በ2 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት በቁ

By Shambel Mihret

August 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመቐለ ከተማ በ2 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ወጪ ግንባታቸው የተጠናቀቁ የአስፋልት መንገዶችና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ ÷ ዛሬ የልማት ፕሮጀክቶቹን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።

አቶ ጌታቸው በስነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት ÷ ዛሬ ለምረቃ የበቁት የልማት ፕሮጀክቶች የውስጥ አቅምን ተጠቅሞ ጥራታቸውን የጠበቁ የልማት ሥራዎችን ጀምሮ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ጥሩ ማሳያ ናቸው።

ከህዝብ ጋር በተቀናጀ መንገድ ከተሰራ ሁሉንም ነገር ማከናወንና ማሳካት እንደሚቻል ጠቅሰው÷ ፕሮጀክቶቹ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የመቐለ ከተማ ከንቲባ ይትባረክ አማሃ በበኩላቸው ÷ በከተማው ለተገነባው የአንድ ኪሎ ሜትር ዋና የአስፋልት መንገድ እና ተጓዳኝ የልማት ሥራዎች 2 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ወጪ ተደርጓል ብለዋል።

ከፕሮጀክቶቹ ምረቃ በተጨማሪ በ35 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የአሸንዳ አደባባይ በ2 ቢሊየን ብር ወጪ ግንባታ ለማካሄድ የመሰረት ድንጋይ መቀመጡን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡