Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የፓኪስታን ወጣቶች የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን እንደሚቀላቀሉ አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፓኪስታን ወጣቶች ሃገር አቀፉን የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንደሚቀላቀሉ አስታውቀዋል፡፡

በነገው ዕለት የሚካሄደው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ይደረጋል፡፡

በዚህም በዕለቱ ብቻ 600 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል መታቀዱም ነው የተገለጸው፡፡

በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ጀማል በከር ÷ በተካሄደው የ2024 የኮፕ-ኢን-ማይ ሲቲ ኮንፈረንስ ላይ ስለ አረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ለወጣቶች ገለፃ አድርገዋል።

በገለጻቸውም ፥ የኢትዮጵያ ህዝብ በነገው ዕለት ብቻ 600 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል የዓለም ክብረ ወሰን ሊያስመዘግብ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ፥ ሀገርን አረንጓዴ ከማልበስ ባለፈ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጡም በላይ በኢትዮጵያ የስራ እድል ፈጠራን ያሳደገ መሆኑንም ተናግረዋል።

የፓኪስታን ወጣቶች የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብርን በማድነቅ በነገው 600 ሚሊየን የችግኝ ተከላ ዘመቻ ላይ እንደሚሳተፉ መግለጻቸውን በፓኪስታን ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version