የሀገር ውስጥ ዜና

በአንድ ጀምበር 600 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል የተያዘው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑ ተገለጸ

By Feven Bishaw

August 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር በአንድ ጀምበር 600 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ያሳየችው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ባለሙያዎች ገለጹ።

ኢትዮጵያ ነገ በምታከናውነው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር 600 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅቷን አጠናቅቃለች።

ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ሙያተኞች እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ለመቋቋም እያከናወነች ያለው ተግባር የሚበረታታ ነው ።

ከአሜሪካ፣ ሴራሊዮን እና ኬንያ የመጡ ባለሙያዎች የመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት÷ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር የጀመረችው ተነሳሽነት ሌሎች ሀገራትን የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።

ይህ ተነሳሽነት በመንግስትና በዜጎች ተግባራዊ እንቅስቃሴ መቀጠሉ አበረታች መሆኑን ጠቅሰው÷ በጎ ዓላማውን ለማስቀጠል የሁሉም ኃላፊነት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት የሰጠችው ትኩረት ትልቅ ለውጥ እያመጣ እንደሚገኝ በመግለጽ÷ ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር 600 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል የያዘቸው ግብ ሁላችንም ትምህርት እንድንወስድ ያደርጋል ብለዋል፡፡