Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያና ኬኒያ በሽብር ቡድን አመራሮችና ታጣቂዎች ላይ የጀመሩትን ኦፕሬሽን ለማጠናከር አቅጣጫ አስቀመጡ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና የኬኒያ የመረጃ ተቋማት በድንበር አካባቢ እና በኬኒያ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድን አመራሮችና ታጣቂዎች ላይ የጀመሩትን ኦፕሬሽን አጠናክረው ለመቀጠል አቅጣጫ አስቀመጡ፡፡

በኬኒያ የመረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ኑረዲን መሐመድ ሀጂ የተመራ ልዑክ ለስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገብቷል፡፡

ልዑኩ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስም የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንን ጨምሮ የአገልግሎቱ አመራሮች አቀባበል አድርገውለታል፡፡

አገልግሎቱ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ÷ የሁለቱ ሀገራት አቻ የመረጃ ተቋማት ከዚህ በፊት በመረጃ ልውውጥ እና በሌሎች የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት የጋር መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው ወደ ስራ መግባታቸው ተገልጿል፡፡

በትብብራቸው መሰረትም የተቋማቱ የስራ ሀላፊዎቸና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ እየተገናኙ ሲገመግሙ መቆየታቸው ተመላክቷል፡፡

በዚሁ መሰረትም የኬኒያ የመረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ኑረዲን መሐመድ ሀጂ ከተቋማቸው ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት  በበርካታ የጋራ አጀንዳዎች ላይ ጥልቅ ውይይት እና ግምገማ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ማስቀመጣቸውን ያስታወቀው አገልግሎቱ÷ ሁለቱ ሀገራት ድንበር እንደሚጋሩት ሁሉ የሚጋሯቸው የደኅንነት ስጋቶች እና አብሮ የመልማት አጀንዳዎች እንዳሏቸው ተጠቅሷል።

በአሁኑ ወቅትም በሀገራቱ ድንበርና በኬኒያ ውስጥ ገባ ወጣ እያለ የተለያዩ እኩይ ተግባራትን የሚፈጽመውን የሸኔ የሽብር ቡድን እንቅስቃሴ ለመግታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

ቡድኑ በተለይም ሲፈጽማቸው የነበሩ ዜጎችን የማገት፣ ንብረት የመዝረፍና የማውደም እንዲሁም የሰዎችን እንቅስቃሴ የማስተጓጎል ተግባር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የኬኒያ ዜጎችንም ጭምር ችግር ላይ መጣሉ ተነስቷል፡፡

ይህን እኩይ ዓላማውን ለማክሽፍ እና ለመግታት የጀመሩትን  የመረጃ ልውውጥ እና  የተቀናጀ  ኦፕሬሽን አጠናክረው ለመቀጠል  መወሰናቸውንም  ነው  የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ ያመላከተው፡፡

በተጨማሪም ቡድኑ የተሰማራባቸውን የኮንትሮባንድ ንግድ፣ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ ህገ ወጥ የማዕድን ማውጣትና ማዘዋወር ስራዎችን ለማስቆም አፋጣኝ ርምጃ ለመውሰድ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢዎች እና በኬኒያ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የሸኔ የሽብር ቡድን በቅርቡ ሁለት የኮሪያ ዜጎችን በማገት ለአልሸባብ አሳልፎ መስጠቱንና ቡድኑ በሶማሊያ ከሚንቀሳቀሰው የአልሸባብ የሽብር ቡድን ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው መሆኑን ያመለከተው መረጃው÷ ሁለቱ የሽብር ቡድኖች በአካባቢው እና በቀጣናው የደቀኑትን  የሽብር  ስጋት በጋራ  ለመከላከልና ለመቀልበስ መወሰናቸውን ገልጿል፡፡

በአካባቢው እና በቀጣናውም ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እያካሄዱ ያሉትን የመረጃ ልውውጥና የተቀናጀ ኦፕሬሽን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የተገለጸው፡፡

በተያያዘም ሁለቱ አቻ የመረጃ ተቋማት በሱዳን ያለው ጦርነት እና አለመረጋጋት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታና ሱዳን ወደ ቀድሞ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ እንድትመለስ በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

የሁለቱም ሀገራት ድንበር ተጋሪ በሆነችው ደቡብ ሱዳንም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና እና የተረጋጋች እንድትሆን በጋራ የማገዝ ስራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተጠቅሷል፡፡

የወቅቱ ስጋት በሆነው የሳይበር ደኅንነት ላይም በጋራ የጀመሩትን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ እንዲሁም በቀጣይም ሊደርስ የሚችል የሳይበር ጥቃትን በጋራ የመከላከልና የማስቆም የተቀናጀ ስራ ለመስራት ተስማምተዋል።

የሀገራት አሁናዊ ስጋት እየሆነ ያለውን የስነ ልቦና ጦርነትን ለመከላከል እና መልሶ ለማጥቃት በሚደረግ ጥረት ሁለቱ አቻ የመረጃ ተቋማት በጋራ ለመስራት መስማማታቸው ተመልክቷል።

በመጨረሻም በኬኒያ የመረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ኑረዲን መሐመድ ሀጂ  የተመራው ልዑክ በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎችን እና የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየምን ጎብኝቷል፡፡

ከጉብኝቱ በኋላ ዳይሬክተር ጄነራሉ በሰጡት አስተያየት÷ የኢትዮጵያ ዋና ከተማና የአፍሪካ ሕብረት መዲና የሆነችው አዲስ አበባ እንደስሟ ውብ እና ማራኪ መሆኗን አይቻለሁ ብለዋል፡፡

Exit mobile version