አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በጎፋ ዞን ደምባ ጎፋ ወረዳ አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል፡፡
ከአቶ አደም ፋራህ በተጨማሪ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ፣ የፌደራል እና የክልል የሥራ ኃላፊዎችም በችግኝ ተከላው ተሳትፈዋል፡፡
አቶ አደም በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላፉት መልዕክት÷ የፊታችን ዓርብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀምበር 600 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል እየተከናወነ ያለው ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ እየሄደ ነው ብለዋል።
ስለሆነም የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች እንዲሁም መላው ኢትዮጵያውያን በዚህ ሀገራዊ አጀንዳ ላይ ያለ ምንም ልዩነት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከችግኝ ተከላው ቀደም ብሎ የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት እና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በጋራ በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት ለተጎዱ ወገኖች የ20 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡