Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአማራ ክልል የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓላት በድምቀት እንደሚከበሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በየዓመቱ የሚከበሩት የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓላት ባህላዊና ሐይማኖታዊ ዕሴታቸውን ጠብቀው በድምቀት እንዲከበሩ ዝግጅት መደረጉ ተገልጿል፡፡

የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ እንዳስታወቀው÷ በአማራ ክልል የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ ከሴ አጨዳና እንግጫ ነቀላ እንዲሁም ሩፋኤል በዓላትን በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቅቋል፡፡

የበዓላቱ ባሕላዊ ክዋኔና ትውፊት ሳይበረዝ ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ በትኩረት እንደሚሰራም ተመላክቷል፡፡

ሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓላትን ለመጪው ትውልድ በሚተላለፍ አግባብ ለማክበር ዝግጅት መደረጉንም የሰሜን ወሎ ዞን ባህልና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ገነት ሙሉጌታ አስታውቀዋል፡፡

በዓላቱ በሰሜን ወሎ በሁሉም ወረዳዎች እና ከተሞች እንደሚከበሩ ጠቁመው÷ ከወትሮው በተለየ ድምቀት ለማክበር ሰፊ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የበዓሉ መከበሪያ ቦታ መረጣና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የገለጹት ኃላፊዋ÷ በዓላቱ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስት መስኅብ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ባህላዊም ሆነ ሐይማኖታዊ በዓላትን ለማክበር ሠላም ወሳኝ በመሆኑ አሁን የተገኘውን ሠላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በዓሉን በተመለከተም የቆቦ እና ላሊበላ ከተማ ወጣቶች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት÷ ከአያት ቅድመ አያቶቻችን ያገኘነው ይህ አኩሪ ባህል ሳይበረዝ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲደርስ የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሻደይ በዓል “ሻደይ ባህላችን ለዘላቂ ሰላማችንና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ሐሳብ እንደሚከበር ተገልጿል፡፡

የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓላት በክልሉ ከነሐሴ 16 ቀን ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ወጣት ሴቶች በተገኙበት በድምቀት እንደሚከበሩ ተጠቁሟል፡፡

Exit mobile version