Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በረሃማነትን በመዋጋት ጥሩ እምርታ ያስመዘገቡ የዓለም ሀገራት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በረሃማነት በዋነኛነት የሚከሰተው በሰዎች እንቅስቃሴና በአየር ንብረት መለዋወጥ ምክንያት ሲሆን÷ በዓማችንም የተለያዩ ሀገራት በረሃማነትን በተሻለ እየተዋጉ እንዳሉ መረጃዎች ያመላክታሉ።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በረሃማነትን ለመዋጋት በተደርገው ጥረት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር 31 ቢሊየን ችግኞችን መትከል መቻሉ ይታወቃል፡፡

አሁን ላይም አብዛኞቹ ችግኞች የፀደቁ ሲሆን÷ በረሃማነትን ተከትሎ ሊከሰት የሚችልን የተፈጥሮ አደጋ ከመከላከል ባለፈ ስነ-ምህዳርን ለግብርና ምቹ በማድረግ በምግብ እራስን ወደ መቻል ለማምራት ማስቻላቸው ይገለፃል፡፡

ሌላኛዋ በረሃማነትን በፅኑ በመዋጋት የምትጠቀሰው ሀገር ቻይና ስትሆን÷ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በቻይና 27 ነጥብ 4 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ መሬት በረሃማ በመሆኑ 4 መቶ ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎችን ለጉዳት ያጋለጠ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

በዚህም ቻይና በፈረንጆቹ 1978 ታላቁ አረንጓዴ ግንብ ፕሮጀክት አማካኝነት በከፍተኛ ሁኔታ ተራቁቶ የነበረውን የጎቢ በረሃ የማልማት መርሐ-ግብር በይፋ ማካሄድ ጀምራለች፡፡

ፕሮጀክቱ እስከ 2050 ድረስ የሚቀጥል ሲሆን÷ በአንዳንድ ቦታዎች 4 ሺህ 800 ኪሎ ሜትር ስፋት ባለውና እስከ 1 ሺህ 400 ኪሎ ሜትር በሚደርስ መሬት ላይ 88 ሚሊየን ሄክታር ያክል ደን ለማልማት መታቀዱ ተነግሯል።

መንግሥት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ትላልቅ የደን ልማት ፕሮጀክቶችን በማካተትና በመደጎም በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ትልቁን የዛፍ መተከል ፕሮጀክት አዎንታዊ ውጤት አስገኝቷል።

ሌላኛው በፈረንጆቹ 2007 ወደ ሥራ የገባው ታላቁ የአፍሪካ አረንጓዴ ግንብ ፕሮጀክት ሲሆን÷ይህም በሳህል ቀጣና በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ኑሮን ለማሻሻል፣ ካርበንን ለማስረግ፣ ግጭትን ለማስወገድ እና ሽብርተኝነትን እና ፍልሰትን ለመቀነስ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

የተመዘገበው ውጤት በቀጣናው ባሉ ሀገራት የተለያየ ቢሆንም ብዙ ሀገራት በተለያዩ ምክንያቶች ወደኋላ ሲቀሩ ኢትዮጵያ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበች ወደ ፊት መገስገሷን የኧርዝ ዶት ኦርግ ዘገባ አመላክቷል፡፡

ዓመታዊ የዝናብ መጠኗ 2 መቶ ሚሊ ሜትር እንደሆነ የሚነገርላት እና በከፍተኛ የበረሃማነት መስፋፋት አደጋ ውስጥ ትገኝ የነበረው ዮርዳኖስም ባካሄደችው በረሃማነትን የመዋጋት እንቅስቃሴ መሻሻሎችን ማስመዝገብ እንደቻለች ይገለፃል፡፡

አውስትራሊያም ደንን በማልማት በረሃማነትን ለመከላከል ባደረገችው ጥረት ከ74 ሚሊየን ሄክታር በላይ ጥብቅ መሬት መለየትና በደን መሸፈን እንደቻለች ተመላክቷል፡፡

ይህም ከሚሰጠው አካባቢያዊ ጠቀሜታ ባለፈ ለመጪው ትውልድ የጤና፣ የትምህርት፣ የምጣኔ ሀብት እና ማህበራዊ ትሩፋቶችን ለማቆየት እንደሚያስችል ተነግሯል፡፡

በኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በየዓመቱ የሚተከሉት ችግኞች ብዛት እያደገ መምጣት መቻሉ ተመላክቷል፡፡

በዘንድሮው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብርም በአንድ ጀንበር 6 መቶ ሚሊየን ችግኞች የሚተከሉ ይሆናል፡፡

Exit mobile version