የሀገር ውስጥ ዜና

ሀገርን ከ1 ሚሊየን በላይ የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ አሳጥቷል የተባለ ግለሰብ ተከሰሰ

By Meseret Awoke

August 21, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ ባንክ ፍቃድ ሳይኖረው የተለያዩ ግለሰቦች ከውጭ ሀገር የሚልኩትን ዶላር በራሱና በተለያዩ ግለሰቦች ስም በማስተላለፍ ሀገር ታገኝ የነበረውን ከ1 ሚሊየን በላይ የአሜሪካን ዶላር አሳጥቷል የተባለ ግለሰብ ክስ ተመሰረተበት፡፡

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የፌደራል ዐቃቤ ህግ በተከሳሹ ላይ በተሻሻለው የባንክ ስራ አዋጅ ቁጥር 1159/2011 አንቀጽ 3 ንዑስ ቁጥር (1)እና አንቀጽ 65 ንዑስ ቁጥር (1) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፏል የሚል ዝርዝር ክስ አቅርቦበታል።

ተከሳሹ ተስፋ ገ/ተክለሀይማኖት የሚባልና ዜግነቱ ኤርትራዊ ሲሆን÷ የመኖሪያ አድራሻው በኦሮሚያ ክልል ሽገር ከተማ ኮዬ ፈጬ ሆኖ ሳለ በነዋሪነት መታወቂያው ላይ የተገለፀው ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 በሚል መሆኑ ተገልጿል፡፡

ይህ ተከሳሽ የባንክ ስራ ለመስራት ከብሔራዊ ባንክ የተሰጠ ህጋዊ ፈቃድ እንደሌለውም ነው የተነገረው፡፡

በዚህም ካልተያዙ ግበረአበሮቹ ጋር በመሆን በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚገኙ ግለሰቦች ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ሲፈልጉ እዚያው ሀገር የሚገኙ ግበረ አበሮቹ ገንዘቡን በመሰብሰብ ፤ የሚላክላቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር የባንክ ሒሳብ ቁጥር እና የገንዘቡን መጠን በሚያስተላልፉለት መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በአቢሲኒያ ባንክ በስሙ በከፈታቸው የሒሳብ ቁጥሮች ከጥር 29 ቀን 2013 ዓ/ም እስከ ሐምሌ 29 ቀን 2014 ዓ/ም ባሉት ጊዜያት በአጠቃላይ 52 ሚሊየን 950 ሺህ 757 ብር ከውጭ ሀገራት ገንዘብ ለተላከላቸው 10 ሰዎች የማስተላለፍ የወንጀል ተግባር መፈጸሙን ዐቃቤ ህግ በክስ ዝርዝሩ ላይ ጠቅሷል፡፡

ይኸውም በባንኮች አልያም በህጋዊ ገንዘብ አስተላላፊዎች አማካኝነት ዶላሩ ቢላክ ኖሮ ሀገሪቱ ታገኝ የነበረውን 1 ሚሊየን 104 ሺህ 468 የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ እንድታጣ ያደረገ መሆኑን ዐቃቤ ህግ ጠቅሶ ያለብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የባንክ ስራ መስራት ወንጀል ክስ አቅርቦበታል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት በዚህ መልኩ በዐቃቤ ህግ የቀረበውን ክሰ ዝርዝር ለተከሳሽ በፍርድ ቤቱ እንዲደርስ ከተደረገ በኋላ ክሱን ለመመልከት ለነሃሴ 20 ቀን 2016 ዓ/ም ተቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ