Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የምድር ድንቅ ስጦታን ከስጋት ለመታደግ …

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምድር ለሰው ልጆች ያበረከተችውን ድንቅ ስጦታ በአግባቡ ጠብቆ ባለማቆየትና ባለመጠበቅ መልሰን እያጣነው ይመስላል፡፡

አካባቢ ማለት በዙሪያችን ያሉት ሕይወት ያላቸውና የሌላቸው ነገሮች ድምር ውጤት ሲሆን ፥ በከባቢው ውስጥ የሚኖረው ሥነ-ፍጥረት መስተጋብሩን ጠብቆ መሄድ ካልቻለ ለኑሮ ዋስትና ስጋት መጋረጡ አይቀሬ ይሆናል።

በዚህ የዓለም አየር ንብርት አሳሳቢ በሆነበት ወቅት፥ስለአሁናዊ ከባቢ ሁኔታ፣ ስለአሳሳቢው የዓየር ንብረት ለውጥና መፍትሄዎቹ፣ ስለምድር መጻዒ እጣ ፈንታና የሰው ልጆች ተጽእኖ እንዲሁም መሰል ጉዳዮች ላይ ዓለም በጥብቅ መወያየት ያስፈልጋታል፡፡

በዚህ ጉዳይ ዓለም በቀጠሮ ቢመክርም ፤ ሀገራት ይሆናል ያሉትን ሃሳብና ገንዘብ ቢያዋጡም አሁን ካለው የዓለም የአካባቢ ሁኔታ ጋር ሲታይ የተደረገው ጥረት በቂ እንዳልሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡

በተለይም ያደጉ ሀገራት በግዙፍ ኢንዱስትሪዎቻቸውና ለአካባቢ ዓየር ብክለት የሚያጋልጡ ተግባሮቻቸውን እንዲገድቡና በአንጻሩ ለችግሩ መፍትሄዎችን እንዲጠቁሙ ግፊት ቢደረግባቸውም የዓለም ከባቢ ንብረት ወደ ስጋት መክተታቸውን ገፍተውበታል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ መከሰት የጎላ ድርሻ ሳይኖራቸው የዓየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል።

እንደአብነትም በቅርቡ የተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ መመልከት ይቻላል፤ አደጋው በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለሞት ተዳርጓል፡፡ጥቂት የማይባሉት በመሬት ውስጥ እንደተቀበሩ ቀርተዋል፡፡

በዚህ ሳቢያም ሃብት ንብረታቸው የወደመባቸው ብዙዎች ናቸው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃም ለጎርፍ፣ ለመሬት መንሸራተት፣ ከፍተኛ ሙቀትና ድርቅ እንዲሁም ሌሎች አደጋዎች ተጋላጭ ሆነዋል።

አደጋዎቹ ማንቂያ ደወል ተደርገው ሊወሰዱና ለመፍትሄውም መንቃት ያስፈልጋል፤በዚህም ወደ ስራ ከተገባ የደረቁ ምንጮች ይፈልቃሉ፤ጥም ያዛላቸው ዕጽዋት ለመስካቸው ውበት ለእንስሳት መኖ ይሆናሉ፤ ዓለም ሚዛኗን ትጠብቃለች፡፡

ሁሉም ሀገር ለዓየር ንብረት ለውጥ የራሱን ጠጠር ሲጥል ዓለም እየደረሰባት ካለና ከሚመጣባት ቅስፈት በትንሹም ቢሆን ታገግማለች፡፡

ለዚህም ኢትዮጵያ ለዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ያጣቻቸውን እስትንፋሶቿን በተለያዩ የንቅናቄ ስራዎች ለመመለስ እየተጋች ሲሆን፤በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን ተክላለች፤ አሁንም አጠናክራ እየሰራችበት ነው።

በተያዘው የክረምት ወቅት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ በቢሊየኖች የሚቆጠር ችግኝ የምትተክል ሲሆን÷የፊታችን ነሐሴ 17 ቀንም በአንድ ጀምበር 600 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ቀጠሮ ይዛለች፡፡

በሰጧት ልክ መልሳ የምትሰጠው ተፈጥሮ በሚደረግላት እንክብካቤና ጥበቃ የተጋረጠውን የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቋቋም ያስችላል።

ኢትዮጵያ እያካወነችው ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም የደን ልማት እና ሌሎች ተያያዠ ጉዳዮች ላይ አመርቂ ወጤት እየታየ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ሆኖም መሰል እንቅስቃሴዎች በጥቂት ሀገራት ብቻ በመደረጋቸው የዓለም የዓየር ንብረት ለውጥ ወደቀደመ ቦታው ሊመለስ እንደማይችል እሙን በመሆኑ፤ ሀገራት እየወሰዱት ያለውን እርምጃ በማጤን ዓለም ከገባችበት ችግር እንድትወጣ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ካደጉ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር በዓየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚደርስባቸው ተጽዕኖ የከፋ በመሆኑ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በእነዚህ ሀገራት ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርግ የአካባቢ ተቆርቋሪ ወገኖች ግፊት እያደረጉ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት የዓየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን አደጋ ለመቋቋም ሲጠይቁት የነበረውንና እየጠየቁት ያለው የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ ተገቢ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊም ነው፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት በተካሄደው የዓለም ምጣኔ ሃብት ጉባዔ ላይ በወጣው ሪፖርት ፥ ዓለም በ2050 በዓየር ንብረት ለውጥ ምክንያት 12 ነጥብ 5 ትሪሊየን ዶላር ስታጣ ፤ ችግሩ የ14 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎችን ሕይወት እንደሚቀጥፍ ተመላክቷል፡፡

በሞቃታማ የዓየር ንብረት ቀጣና ባሉ ሀገራት የሚኖሩ 500 ሚሊየን ያህል ሰዎችም በዚሁ በሚዛመቱ እንደ ወባ፣ ዴንግ እና ዚካ ያሉ በሽታዎች እንደሚጠቁ ነው የተጠቆመው፡፡

ሪፖርቱ ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር ይመዘገባል ብሎ የተነበየው ከጎርፍ እና ከድርቅ የተፈጥሮ አደጋዎች ጋር ተያይዞ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ዓለም 12 ነጥብ 5 ትሪሊየን ዶላሩን የምታጣው ከሙቀት መጨመር፣ ድርቅ እና የጎርፍ አደጋ ጋር በተገናኘ በምታስተናግደው የምጣኔ ሃብት ተፅዕኖ መሆኑንም ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡

ተፅዕኖው በቀዳሚነት የእስያ ሀገራትን ሲጎዳ አውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ በሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ገፈት ቀማሽ እንደሚሆኑም ሪፖርቱ አስገንዝቧል፡፡

በዓየር ንብረት ለውጥ የእስያ ሀገራት 3 ነጥብ 5 ትሪሊየን፣ አውሮፓ 2 ነጥብ 6 ትሪሊየን እንዲሁም ደቡብ አሜሪካ 2 ነጥብ 2 ትሪሊየን ዶላር ጉዳት ይደርሳል ተብሏል፡፡

በዚህም በቀደሙት የዓየር ንብረት ለውጥ ስብሰባዎች የተደረሱ ስምምነቶች በአስቸኳይ ከተተገበሩና የአየር ንብረት ለውጥ መንስኤዎችን ለመግታት ሙከራ ከተደረገ የምድርን ደህንነት ማስጠበቅ ይቻላል።ምድርም ባደረግንላት ጥበቃና እንክብካቤ ልክ መልሳ ትሰጠናለች።

በመሰረት አወቀ

Exit mobile version