Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያና የመን የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና የመን ያላቸውን ታሪካዊ የሁለትዮሽ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ተስማምተዋል፡፡

በኳታር፣ ኢራን እና የመን የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፈይሰል ከየመን ፕሬዚዳንታዊ ም/ቤት ሊቀ መንበር ራሽድ ሙሐመድ አል-አሊሚ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ ኢትዮጵያ እና የመን ለረጅም ጊዜያት የዘለቀ ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተዋል።

ራሽድ ሙሐመድ (ዶ/ር) የመናውያን ችግር ሲያጋጥማቸው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚሰደዱ ጠቅሰው ÷ ኢትዮጵያውያን ለሚያደርጉት አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ለየመን ሰላምና መረጋጋት በጋራ መስራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

አምባሳደር ፈይሰል በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ለያዘችው የእድገት እና የብልፅግና ጉዞ የየመን ሰላምና መረጋጋት ለአጠቃላይ የቀጣናው መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን አውስተዋል፡፡

በቀጣናው የሚፈልገውን ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት ኢትዮጵያ ያላሰለሰ ጥረት እንደምታደርግም አብራርተዋል::

ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያና የመንን የቆየ ታሪካዊ ወዳጅነትና የሁለትዮሽ ትብብር ለማጎልበት እንዲሁም በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ መስኮች ያላቸውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ተስማምተዋል፡፡

አምባሳደር ፈይሰል በወቅቱ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለየመን ፕሬዚዳንታዊ ም/ቤት ሊቀ መንበር ማቅረባቸውንም የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version