አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዛሬ በተጀመረው ዓለም አቀፉ የቡድን 20 ሀገራት የእምነት ተቋማት ፎረም የ2024 አመታዊ የምክክር መድረክ ላይ እየተሳተፈ ነው፡፡
በብራዚል እየተካሄደ በሚገኘው የምክክር መድረክ የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እየተሳተፉ ነው፡፡
በመድረኩ የተለያዩ ሀገራት የሐይማኖት መሪዎች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅት መሪዎች፣ የሴቶችና ወጣት የሥራ ሃላፊዎችና ተወካዮችም ተሳትፈዋል፡፡
የሐይማት ተቋማት አብዛኛውን ማህበረሰብ የሚወክሉ፣ የሚያገለግሉ እና ሰዎች መልካም ሕይወት እንዲሁም ኑሮ መምራት ይችሉ ዘንድ በየቀኑ ከፍ ያላ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ተቋማት መሆናቸው በመድረኩ ተገልጿል፡፡
በተለይም በመንፈሳዊ ሕይወት፣ በጤና፣ በትምህርት፣ ግጭትን በመከላከል፣ ሰላምን በመገንባት፣ በልማት፣ የፖሊሲ ግብዓት በመስጠትና ፖሊሲዎች በተሟላ ሁኔታ ይተገበሩ ዘንድ ድምፅ በመሆን የማይተካ ሚና ይጫወታሉ ተብሏል፡፡
የዘንድሮው የቡድን 20 ሀገራት የእምነት ተቋማት ጉባኤ በሰላም ግንባታ፣ በእዳ ስረዛ፣ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ውይይት እንደሚያደርግ ተመላክቷል፡፡
እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመቀነስና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ጉባኤው ከመከረ በኋላ የጋራ አቋም ላይ እንደሚደርስ ይጠበቃል መባሉን ከሐይማኖት ተቋት ጉባዔ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ከመድረኩ ጎን ለጎን ከዓለም አቀፍ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎችና ከልዩ ልዩ ድርጅት ኃላፊዎች ጋር መምከራቸው ተገልጿል፡፡