Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከተረጅነት ለመውጣት በሚደረገው ጥረት የሴፍትኔት ፕሮግራምን በሽግግር ራስን ለመቻል መጠቀም ይገባል- አምባሳደር ሽፈራው (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከተረጅነት ለመውጣት በሚደረገው ጥረት የሴፍትኔት ፕሮግራምን በሽግግር ራስን ለመቻል መጠቀም እንደሚገባ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ገለጹ፡፡

በገጠር ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በ1997 ዓ.ም የተጀመረው የልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ከ8 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ እንዳደረገ ተገልጿል፡፡

አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ ከተረጅነት አስተሳሰብ መውጣት ሲባል በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችን መርዳት ይቆማል ማለት አይደለም፡፡

የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ ሲፀድቅ ሰብዓዊ ድጋፍን ማቆም ሳይሆን ለሚገባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተገቢ ድጋፍ እንዲደርስ ማድረግን ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ሀገር በሰብዓዊ ድጋፍ ሰበብ ቋሚ ተረጂ የመሆን አባዜ 50 ዓመታትን ተሻግሯል ያሉት ኮሚሽነሩ÷ ከተረጅነት አስተሳሰብ ለመውጣት ጸጋዎችን ማልማትና የሴፍትኔት መርሐ ግብርን ማጠናከር እንደሚገባ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያን ከተረጅነት የመውጣት ትልም ለማሳካት የሴፍትኔት መርሐ ግብርን ማጠናከር አጋዥ እንጂ እንቅፋት ሊሆን አይችልም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሴፍትኔት መርሐ ግብርን ላልተገባ አላማ የሚጠቀሙ አካላት እንዳሉ ጠቁመው÷ በራሳቸው ሰርተው መለወጥ የሚችሉ ግለሰቦች ቋሚ መጦሪያ ሊያደርጉት እንደማይገባ አስገንዝበዋል፡፡

Exit mobile version