Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኤምባሲው ለጠቅላይ ፍርድቤት ከ300 ሺህ ዶላር በላይ የሚገመት ድጋፍ አበረከተ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከ300ሺህ ዶላር በላይ የሚገመት የስማርት ኮርት ሩም የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ድጋፍ አበረከተ፡፡

ኤምባሲው ድጋፉን ያደረገው በዓለም አቀፍ የናርኮቲክና ሕግ ማስከበር ጉዳዮች ቢሮ በኩል መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ድጋፋም ፥ 13 ስማርት ኮርት ሩም የሚያገለግሉ ኮምፒውተሮች፣ ካሜራዎች፣ መቅረጫ ቁሶች እና ስማርት ቲቪዎችን ያካተተ ከ300ሺህ ዶላር በላይ የሚገመት የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን ናቸው ተብሏል፡፡

የቴክኖሎጂ መሳሪያዎቹን ያበረከቱት አምባሰደር ኤርቪን ማሲንጋ በዚህ ወቅት ÷ ፍርድ ቤቱ የጀመረውን የለውጥ ጉዞ አድንቀው ፤ የአሜሪካ መንግስት እነዚህን ውጥኖች ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን መግለጻቸውን ከኢምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ቀልጣፋ የፍርድ ቤት ሥርዓቶች ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር፣ ተጠያቂነትን፣ ግልፅነትንና ፍትሃዊነትን ለማጎልበት ወሳኝ በመሆናቸው የፍርድ ቤት አመራሮች የፍርድ ቤት ማዘመን ላይ በትኩረት መስራታቸውን በመቀጠል በመላ ሀገሪቱ የስማርት ፍርድ ቤት አገልግሎቶች እንዲስፋፋ ያላቸውን ምኞትም ገልጸዋል።

የተደረገው ድጋፍም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ከማጠናከር ባሻገር የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጥ በዲጂታል ዘዴ የታገዘ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡

አምባሰደር ኤርቪን ማሲንጋ በፍርድ ቤቱ የሚገኙትን የስማርት ኮርት ሩሞችንና የዋይድ ኤሪያ ኔትወርክ ዳታ ሴንተርን የጎበኙ ሲሆን ፥ በቀጣይ በጋራ ስለሚሰሩባቸው የትብብር መስኮችም ውይይት አድርገዋል፡፡

Exit mobile version