አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሃማስ የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነትን የሚያደናቅፉ አለመግባባቶችን ለመፍታት የቀረበውን ሃሳብ እንዲቀበል አሜሪካ አሳስባለች፡፡
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በትናንትናው ዕለት ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ብሊንከን የእስራኤል ቆይታቸውን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ÷ እስራኤል በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነትን የሚያደናቅፉ አለመግባባቶችን ለመፍታት ዋሽንግተን ያቀረበችውን አሻጋሪ ሀሳብ እንደተቀበለች ተናግረዋል፡፡
በተመሳይ ሃማስም የቀረበውን ሃሳብ እዲቀበል አሳስበው÷ ይህ ግፊት ስምምነት ለማድረግ ከሁሉ የተሻለ እና ምናልባትም የመጨረሻው አጋጣሚ ሊሆን እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በአሜሪካ፣ በግብፅና ኳታር አሸማጋይነት የገቡትን ቃል ተግባራዊ በሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ ግልፅ የሆነ መግባባት ላይ በመድረስ ሒደቱን ማጠናቀቅ እንደሚገባቸውም አፅንኦት ሰጥተዋል።
ባለፈው ሳምንት በኳታር የተካሄደው የተኩስ አቁም እና ታጋቾችን የመለዋወጥ ውይይት ያለምንም ስምምነት መቋረጡን ጠቁመዋል፡፡
ይሁን እንጂ በእስራኤልና በሃማስ መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብ በአሜሪካ በቀረበው ሃሳብ መሰረት ውይይቱ በዚህ ሳምንት ይቀጥላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
ብሊንከን ጉብኝቱን ለማድረግ የተገደዱት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በግጭቱ ላይ ያላቸው አቋም በምርጫ ሒደቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ስላሳደረባቸው መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ዴሞክራት ፓርቲ በትናንትናው ዕለት ብሔራዊ ጉባዔውን ሲጀምር÷ የፍልስጤም ደጋፊዎች፣ ሙስሊሞች እና ዓረብ አሜሪካውያን የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡
በሌላ በኩል የፍልስጤም ጽንፈኛ ቡድን ከብዙ ዓመታት በኋላ በእስራኤል ውስጥ ዳግም የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት መፈፀሙን በማስታወቅ ለተከሰተው ፍንዳታ ሃላፊነቱን ወስዷል፡፡
በአንጻሩ እስራኤል የወሰደችው ወታደራዊ ጥቃት በጋዛ 30 የሚደርሱ ፍልስጤማውያን ለህልፈት መዳረጋቸውን የሕክምና ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
ይህ ሁሉ ድርጊትም መሬት ላይ ጥቂት የእርቅ ምልክት ሊኖር እንደሚችልና በሌላ በኩል ደግሞ ጦርነቱ ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት ማጫሩን ሬውተርስ ዘግቧል፡፡