የሀገር ውስጥ ዜና

የ2024 የአፍሪካ ሕብረት መሪ ቃልን አስመልክቶ የተዘጋጀ መድረክ እየተካሄደ ነው

By Amele Demsew

August 20, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ሕብረት የ2024 የትምህርት መሪ ቃል አከባበርን በማስመልከት የተዘጋጀ መድረክ በሕብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።

መድረኩን የአፍሪካ ሕብረት የልማት ኤጀንሲ (አውዳ-ኔፓድ) እና የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የልማት አጋሮች ጋር በመሆን ነው ያዘጋጁት።

ዝግጅቱ “ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ ማስተማር፤ የማይበገሩ የትምህርት ሥርዓቶች በመገንባት በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ፣ የሕይወት ዘመን፣ ጥራትና አግባብነት ያለው የትምህርት ተደራሽነትን ማስፋት” በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ነው።

እስከ ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆየው የአከባበር መርሐ ግብር ትምህርት፣ ቴክኖሎጂና ዓለም አቀፍ ትብብር ለአፍሪካ ልማት ያለው አበርክቶ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በ21ኛው ክፍለ ዘመን ተደራሽነት፣ ጥራትና ማህበራዊ ጠቃሜታ ያለው የማይበገር የትምህርት ስርዓት በአፍሪካ መገንባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር እንደሚደረግ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተለይም የሰው ሰራሽ አስተውሎትና ዓለም አቀፍ አጋርነቶች ለከፍተኛ ትምህርት እድገት ያላቸው አስተዋጽኦ በአከባበሩ ላይ እንደሚዳሰስም ተጠቁሟል።

ዝግጅቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ባለሙያዎችና ፖሊሲ አውጪዎች በአፍሪካ የቴክኖሎጂና ሳይንስ መጻኢ ሁኔታ ላይ የሚወያዩበት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ተገልጿል።