Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሕክምና ኮሌጁ የመካንነት ሕክምና አገልግሎትን ለማስፋት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የሥነ-ተዋልዶ ሕክምና ማዕከል የመካንነት ሕክምና አገልግሎቱን ለማስፋት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

የመካንነት ችግር ለመቅረፍ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ አምስት የሥነ-ተዋልዶ ሕክምና ማዕከል በአዲስ አበባ ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ ነው።

ላለፉት አምስት ዓመታት በአገልግሎቱ ከ50 ሺህ የሚበልጡ ዜጎች የተለያዩ ሕክምና እያገኙ መሆኑን በሕክምና ኮሌጁ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ክፍል የመካንነት ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ሙስጠፋ ነጋሽ ይገልጻሉ።

ከእነዚህም ውስጥ ከ1 ሺህ 500 የሚበልጡ ጥንዶች በአይ ቪ ኤፍ ሕክምና (የአይ ቪ ኤፍ ሕክምና የሴቷን እንቁላል በመውሰድና የወንዱን የዘር ፈሳሽ በመውሰድ በላቦራቶሪ ጽንሱ ከተፈጠረ በኋላ ወደ ማህጸን የመመለስ ሕክምና ነው) ልጅ ማግኘት መቻላቸውን ጠቅሰዋል።

ይህንን የመካንነት ሕክምና ለመውሰድ የሚመጡ ጥንዶች ሴቷ እድሜዋ ከ35 ዓመት በታች የሚሆን ከሆነ ሕክምናው የተሳካ እንዲሆን በእጅጉ እንደሚያግዝ ገልጸው ፥ የመራቢያ አካል ሁኔታዎችም ለህክምናው ስኬት ሌላኛው ምክንያት መሆናቸውንም አንስተዋል።

ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በኋላ ወደ ውጭ ሄደው ሕክምናውን የሚያደርጉ ጥንዶችን አገልግሎቱን በሀገራቸው እንዲያገኙ ማድረግ ማስቻሉንና ለበርካታ ጎረቤት ሀገራት ጭምርም የህክምና አገልግሎቱን መስጠት መቻሉን መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

ማዕከሉ አሁን ላይ ወደ አምስት ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን ÷ በቀጣይ በክልሎች ቅርንጫፎችን በመጨመር የአገልግሎት አድማሱን ለማስፋት እንደሚሰራ ተናግረው ፤ ለዚህም የመድኃኒት አቅርቦቱንና የሕክምና መሳሪያዎች የማሟላት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጥንዶች ለአንድ ዓመትና ከዚያ በላይ የወሊድ መከላከያ ሳይጠቀሙ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት እየፈጸሙ ፅንስ መፍጠር ካልቻሉ ቢያንስ በአንዳቸው ላይ የመካንነት የጤና እክል መኖሩን እንደሚያሳይ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስድስት ሰዎች በአንዱ መካንነት እንደሚያጋጥም ድርጅቱ ገልጿል።

Exit mobile version