ዓለምአቀፋዊ ዜና

ሞዛምቢክ የናካላን ወደብ ለማላዊ ለማከራየት ተስማማች

By Melaku Gedif

August 19, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሞዛምቢክ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኘውን የናካላ ወደብ፣ ወደብ አልባ ለሆነችው ጎረቤቷ ማላዊ ለማከራየት መስማማቷ ተገልጿል፡፡

የወደብ ኪራይ ስምምነቱን የሞዛምቢክ ፕሬዚዳንት ፊሊፔ ኒዩሲ እና የማላዊ አቻቸው ላዛሩስ ቻክዌራ ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ትስስር ይበልጥ ማጠናከር እንደሚያስችል ነው የተገለጸው፡፡

ከዚህ ባለፈም ስምምነቱ ለሞዛምቢክ የወደብ ኪራይ ገቢ የሚያስገኝ ሲሆን÷ ማላዊ ደግሞ አዲስ የእቃ ማጓጓዣ ወደብ እንድታገኝ ያስችላታል ተብሏል፡፡

የሞዛምቢክ ፕሬዚዳንት ፊሊፔ ኒዩሲ÷ስምምነቱ እንደ ሞዛምቢክ-ማላዊ የጋራ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አይነት ጅምር ፕሮጀክቶችን ያግዛል ብለዋል፡፡

የማላዊ ፕሬዚዳንት ላዛሩስ ቻክዌራ በበኩላቸው÷ የናካላ ወደብ ማላዊ እቃ ለማጓጓዝ የምታወጣውን ወጪ በእጅጉ እንደሚቀንስ ተናግረዋል፡፡

የናካላ ወደብ በማላዊ፣ ዛምቢያ እና ሞዛምቢክ በጋራ እየተገነባ የሚገኝ የናካላ ልማት ኮሪደር አካል ሲሆን÷የፕሮጀክቱ ዋና አላማ ወደብ አልባ የሆነችውን ማላዊ ለማገዝ እና የቀጣናውን የልማት ትስስር ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ኮሪደሩ በአጠቃላይ 722 ማይል የመንገድ ግንባታ ያለው ሲሆን÷ ወደ ማላዊ ዋና ከተማ ሊሎንግዌ የሚያገናኝ የባቡር መስመር ጥገና እንዲሁም የፍተሻ ኬላዎች አሉት መባሉን ዘ ማሪታይም ኤክስኪዩቲቭ ዘግቧል፡፡