Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የገበያ ዕድሎችን ማሳደግ እንደሚያስችል ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የእሴት ሰንሰለትንና የገበያ ዕድሎችን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ከኢትዮጵያ ወደ ሕንድ የሚላኩ የቅባት እህሎች፣ የጥራጥሬ እና የቡና ምርት የወጪ ንግድ ላይ ባሉ መልካም ዕድሎች ዙሪያ በሁለቱ ሀገራት የተዘጋጀ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)÷ጥናቱ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ትስስር የሚያጠናክርና ኢትዮጵያ እያከናወነች ላለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ምርታማነትን፣ የእሴት ሰንሰለትንና የገበያ ዕድሎችን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር አኒል ኩማር በበኩላቸው÷የሕንድ ኤምባሲ የሁለቱን ሀገራት የወጪ ንግድ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተካሄደው ጥናት የቅባት እህሎች፣ የጥራጥሬ፣ የጥጥ እና የቡና ምርቶች ላይ የሚከናወነውን ንግድ ለማጠናከር እንደሚያግዝ መጥቀሳቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version