አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም በቴሌ ብር ሱፐር አፕ አማካኝነት ቪዛ ካርድን መጠቀም የሚያስችል አገልግሎት በይፋ አስጀምሯል።
አገልግሎቱን ኢትዮ ቴሌኮም፣ ቪዛ ካርድ እና አቢሲኒያ ባንክ በዛሬው ዕለት በጋራ አስጀምረውታል፡፡
ቪዛ ዳይሬክትና ቴሌብር ሬሚት አፕን በቴሌብር ሱፐር አፕ በማውረድ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚቻል ተገልጿል።
አገልግሎቱ በ190 ሀገራት የሚኖሩ ዜጎች የቪዛ ዳይሬክትን ተጠቅመው በቀላሉ ብር መላክ እና መቀበል የሚችሉበት መሆኑ ተገልጿል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ÷ አገልገሎቱ ዜጎች በየትኛውም ሀገር ሆነው የእጅ ስልካቸውን በመጠቀም ገንዘብ የሚልኩበትና የሚቀበሉበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህም ወደ ሀገር ውስጥ የሚላከውን የገንዘብ መጠን (ሬሜታንስ) እንደሚያሳድገው ነው የገለጹት፡፡
በቅድስት አባተ