አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሁኑ ወቅት የዓለም የጤና ስጋት ተብሎ በዓለም ጤና ድርጅት የተፈረጀው የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ በዝንጀሮ በጂነስ ኦርቶፖክስ ቫይረስ የሚመጣ ተላላፊ በሽታ ነው።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ተላላፊ ህመም ሲሆን÷ በሽታው ካለበት ሰው ወይም እንስሳ በንክኪ ሊይዘን ይችላል።
በበሽታው ከተያዘ ሰው የመተንፈሻ አካላት ብናኞች፣ የቆዳ ቁስል ወይም የሰውነት ፈሳሾች አማካኝነት በቅርብ ንክኪ፣ መሳሳም፣ መተቃቀፍ፣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት እና በቆዳ ለቆዳ ንክኪ ይተላለፋል።
እንዲሁም በበሽታው የተያዘ ሰው ተጠቅሞባቸው ከተበከሉ አልባሳት፣ የቤት እቃዎችንና ሌሎች ግኡዝ ነገሮችን በመንካት ሊተላለፍ ይችላል፤ ነፍሰ ጡር እናቶች ቫይረሱን ወደ ጽንሱ ሊያስተላልፉ ይችላሉ።
የበሽታው ምልክቶች መታየት የሚጀምሩት አንድ ሰው ለቫይረሱ ከተጋለጠ ከሳምንት በኋላ ሲሆን÷ አንዳንዴ በቶሎ ወይም ሌላ ጊዜ ዘግየት ብሎ ሊጀምር ይችላሉ።
የተለመዱ የበሽታው ምልክቶች ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የእጢ እብጠት፣ የመገጣጠሚያ ህመምና ድካም ጨምሮ ቆዳ ላይ የሚወጣ ቁስል (ሽፍታ) ዋነኛ መገለጫው ነው።
ይህ የቆዳ ምልክቶች መጀመሪያ ላይ ጠፍጣፋ ቀላ ያለ ሽፍታ ሆኖ ይጀምርና ከዚያ አብጦ ፈሳሽ ይቋጥራል፤ በመቀጠልም ይፈርጥና ይቆስላል።
ይህ ቁስል በፊት ላይ፣ በአፍ ውስጥ እና እንደ እጆች፣ እግር፣ ደረት፣ የመራቢያ አካላት ወይም ፊንጢጣ ያሉ ሌሎች የአካል ክፍሎች ላይ ሊወጣ ይችላል።
ቁስሉ ሲቆይ ይደርቅና ተቀርፎ ይወድቅና በቦታው አዲስ ቆዳ ይተካል።
ከላይ የተጠቀሱትን ምልክቶች የሚያሳይ ማንኛዉም ሰዉ በሚገኝበት ጊዜ በአቅራቢያ ወደሚገኝ የጤና ተቋም ሪፖርት እንዲያደርግ ወይም በ952 እና 8335 ነጻ የስልክ መስመር ጥቆማ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
በኢትዮጵያ እስካሁን በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተጠረጠረም ሆነ የተረጋገጠ ታማሚ እንደሌለ ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የተለያዩ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን የቅድመ ዝግጅት፣ የቅኝት እና የምላሽ እንዲሁም የድንበር ጤና ልየታ እና አገልግሎት ስራዎችን የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ማስተባበሪያና ምላሽ ማዕከል በማቋቋም እየተሰራ ነው፡፡
በ13 የአፍሪካ ሀገራት 2 ሺህ 863 ሰዎች በበሽታ መያዛቸው እና 517 ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸዉ የተረጋገጠ ሲሆን÷ በሽታውም የህብረተሰብ ጤና አህጉራዊ ደህንነት ስጋት መሆኑ ተገልጿል፡፡
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ በዴንማርክ (በፈረንጆቹ 1958) በዝንጀሮዎች ውስጥ የተገኘ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ በሰው ልጅ ላይ የተገኘው በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ነው፡፡
ተጨማሪ መረጃ የአዲስ አበባ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ