የሀገር ውስጥ ዜና

ሕዝቦቻችንን በማስተባበር ፈጣን የሆነ ልማት ለማስመዝገብ እንሰራለን – ወ/ር አለሚቱ ኡሞድ

By Meseret Awoke

August 18, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕዝቦቻችንን በማስተባበር ፈጣን የሆነ ልማት ለማስመዝገብ በትኩረት እንሰራለን ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ገለጹ፡፡

በጋምቤላ ክልል አዲስ የተሾሙት ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ እና ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሏክ ሮን (ዶ/ር) የሕዝብ ለሕዝብ የሰላም ግንኙነት ሥራዎችን ማከናወን ጀምረዋል።

በዚህ ሰመረትም በጋምቤላ ከተማ 01 እና 03 ቀበሌዎች ሕዝቡ ባዘጋጀላቸው የእንኳን ደህና መጣችሁ እንዲሁም የትውውቅና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መድረክ ላይ መታደማቸው ተገልጿል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ ሕዝቦቻችንን በማስተባበር ፈጣን የሆነ ልማት ለማስመዝገብ እንሰራለን።

ለልማት መኖር ሰላም ወሳኝ በመሆኑ በተለይም ማህበራዊ ችግሮቻችንን በመመካከር እና መፍትሄ በማበጀት ወጣቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች ይሰራሉ ብለዋል።

ስንኖር ሰላምን ልናስቀድም ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሯ÷ የሚያለያዩ ሳይሆን ሊያስተሳስሩን የሚችሉ እሴቶችን መገንባት ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

ለሰላም ግንባታ የዕምነት ተቋማት ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ፥ ተቋማቱ ለክልሉ ዘላቂ ሰላም እያደረጉ ያሉትን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሏክ ሮን(ዶ/ር) በበኩላቸው አመራርነት የበርካታ ሕዝቦችን ኃላፊነት መረከብ መሆኑን ገልጸው ፥ ለክልሉ ሰላምና ብልፅግና በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

ዕምነት ያለው ሕዝብ ይተባበራል ፤ይከባበራል እንዲሁም ተቻችሎ ይኖራል ፤ በክልሉ የሚኖሩ ሕዝቦች ይህንኑ ተግባር ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ክልሉ በቂ ሃብት ያለው በመሆኑ ግጭትንና መገፋፋትን በመተው በጋራ ማልማት አለብን ሲሉም መልዕክት ማስተላለፋቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።