አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዩክሬን በኩርስክ የኒውክሌር ሃይል ማመንጫ ማዕከል ላይ ጥቃት ከሰነዘረች የሩሲያ ጦር አፋጣኝ አጸፋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስጠንቅቋል።
ዩክሬን ከቀናት በፊት ወደሩሲያ ግዛት ዘልቃ በመግባት ጥቃት እያደረሰች መሆኗን እና በኩርስክ ግዛትም ድል እየቀናት መሆኑን ገልጻለች፡፡
ይህን ተከትሎም ዩክሬን እና ሩሲያ በግዙፉ ዛፖሪዝዝሂያ የኒውክሌር ሃይል ማመንጫ ማዕከል ላይ ተነስቶ በነበረው የእሳት አደጋ ምክንያት እርስ በርስ ተወነጃጅለው እንደነበር ይታወሳል፡፡
በዚህም የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ፥ በሩሲያ ከሁለት ዓመት በላይ ሲተዳደር የነበረው የኒውክሌር ሃይል ማመንጫ ማዕከል እሳት እንዲነሳ ምክንያቷ ራሷ ሞስኮ ናት ሲሉ ወንጅለዋል፡፡
በአንጻሩ ሩሲያ የኒውክሌር ማዕከሉ በእሳት እንዲያያዝ ያደረገችው ዩክሬን ናት ስትል መወንጀሏየሚታወስ ነው፡፡
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ÷ በሁለቱ ሀገራት መካከል እየከረረ በመጣው ጦርነት የኩርስክን የኒውክሌር ጣቢያ ለማጥቃት ዩክሬን አቅዳለች ብሏል፡፡
በዚህም ዩክሬን የኒውክሌር ማዕከሉን ለማጥቃት ካሰበች ከባድ አጸፋዊ ምላሽ ይጠብቃታል ሲል ማስጠንቀቁን አርቲ ዘግቧል፡፡
ዩክሬን እያደረገች ያለው ትንኮሳም ሩሲያን ተጠያቂ ለማድረግ በማሰብ መሆኑን ሚኒስቴሩ አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
የኒውክሌር ጣቢያው ላይ ጥቃት ከተፈጸመ የጨረር ልቀትና የኒውክሌር አደጋ በመላው አውሮፓ ሊከሰት እንደሚችል ተመላክቷል፡፡