የሀገር ውስጥ ዜና

ተቋማቱ አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ

By Shambel Mihret

August 18, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስቴር እና የገቢዎች ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት የችግኝ ተከላ በማካሄድ አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ።

ተቋማቱ ‘የምትተክል ሀገር፤ የሚያጸና ትውልድ’ በሚል እየተካሄደ በሚገኘው የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተሳትፎ በማድረግ ችግኝ ተክለዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ ሃላፊዎችና ሰራተኞች በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ማና ወረዳ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካሂደዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ፤ በጅማ ዞን እየተካሄዱ ያሉ የግብርና ስራዎች የመንግስት የዘርፉ ዕቅድ እየተሳካ መሆኑን ያሳዩ ናቸው ብለዋል።

በዞኑ በዚህ ክረምት የሻይ ቅጠል ችግኝን ጨምሮ የተለያዩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተተከሉ ተስፋሁን ከበደ ዘግቧል።

በተመሳሳይ የገቢዎች ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራርና ሰራተኞች በአፋር ክልል ዱብቲ ወረዳ ገበለላይቱ ጣቢያ ላይ አረንጓዴ ዓሻራቸውን አኑረዋል።

የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ በወቅቱ እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ትኩረት ሰጥታለች።

ተግቶ ከተሰራ የአፋር ሰፋፊ መሬቶችን ማልማት እንደሚቻል ማሳያዎች እንዳሉ ያነሱት ሚኒስትሯ፤ ዛሬ ከተተከሉት ችግኞች መካከል ምርቶቹን ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ሊያስገኙ የሚችሉ እንዳሉበት አንስተዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተሰሩ ሥራዎች ለውጦች ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።