አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በፋይናንስ ኢንቨስመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት እንዳሳደረባቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ አቅራቢ ኩባንያዎች (ፋይንቴክ) ገለጹ።
የፋይናንስ ተቋማት ቴክኖሎጂ አቅራቢና አማካሪ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች÷ ኢትዮጵያ በፖሊሲ ማሻሻያ ላይ የወሰደቸው እርምጃ ይበል የሚያሰኝ መሆኑንም ገልጸዋል።
”ፊናክል ሶሉሺን” የተሰኘው የሕንዱ ዓለም አቀፍ የባንክ አማካሪ ኩባንያ ሃላፊ ናሬሽ ብሀኖትራ÷ የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለምጣኔ ሃብቷ ዘላቂ እድገት መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።
የዘርፉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችም መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ በር የሚከፍትና ለሀገር በቀልና ለውጭ ፋይናንስ ተቋማት የጋራ ትብብር፣ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር የሚፈጠር መሆኑን ገልጸዋል።
በፋይናንስ ተቋማት ትስስር ላይ የሚሰራው የዓለም ስትራቴጂክ ጥምረት ማዕከል የስትራቴጂ ትብብር ኃላፊ መሐመድ ቶፊቅ÷ በርካታ ታዳጊ ሀገራት ያደረጉት የፖሊሲ ማሻሻያ ለኢኮኖሚ ዕድገት ምህዋር ሆኗቸዋል ብለዋል፡፡
መሰረቱን ደቡብ አፍሪካ ያደረገው የ”ኢ ኤፍ ቲ” ኮርፖሬሽን ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክላይተን ሀይዋርድ በበኩላቸው÷ ኩባንያው ለዲጂታል ባንክ አገልግሎት የሚበጁ ቴክኖሎጂዎችን የሚያቀርብ መሆኑን አንስተዋል።
ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ መፈቀዱ ለአካታች ፋይናንስ ስርዓት ትግበራ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ዘመኑን በዋጁ ቴክኖሎጂዎች ታግዘው በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ ያደርጋል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
በአብዛኛው የዓለም ሀገራት አገልግሎት የሚሰጠው ኬኒያ በቀሉ የ”ካስፐርስኪ” ዓለም አቀፍ የዲጂታል ባንክ ቴክኖሎጂ አቅራቢ ኩባንያ ሽያጭ ኀላፊ ቤተል ኦፒልም ይህን ሃሳብ ይጋራሉ።
‘ኪኤምፒጂ” የተሰኘው ሌላው የባንክ ቴክኖሎጂ አቅራቢ ድርጅት የቴክኖሎጂ ሽግግር ክፍል ዳይሬክተር ማቲን ኪማኒ÷ የአፍሪካ ሀገራት በትስስር እንጂ በተናጠል ዘላቂ ዕድገት ማምጣት የማይችሉ መሆኑን አንስተዋል።
በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ለሚንቀሳቀሱ የፋይናንስ ተቋማት የበለጠ ትስስር እንዲፈጥሩ እና ድንበር ዘለል ተደራሽነት እንዲያሰፉ ያስችላል ሲሉም ተናግረዋል።