አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ በማራቶን ውድድሩ ጉዳት ቢያጋጥመኝም የሀገር ፍቅር ስሜት ርቀቱን እንድጨርስ አድርጎኛል ሲል አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ገለፀ፡፡
አትሌት ታምራት ቶላ ባሸነፈበት የፓሪሱ የማራቶን ውድድር ላይ የተሳተፈው ቀነኒሳ በቀለ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ÷በማራቶን ውድድሩ 10 ኪሎ ሜትሮችን ከሮጠ በኋላ የጡንቻ መሸማቀቅ እንዳጋጠመው ገልጿል፡፡
ከ15 ኪሎ ሜትር በኋላ ሩጫውን ለማቆም አስቦ እንደነበር ገልፆ÷ነገር ግን ለሀገሬ ያለኝ ፍቅር ህመሙን ችዬ ርቀቱን እንድጨርስ አድርጎኛል ብሏል፡፡
ኦሊምፒክ ሜዳሊያዎችን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ጽናት እና ቁርጠኝነት የሚታይበት መድረክ መሆኑን የገለፀው አትሌቱ ÷አሁን ላይ ህክምና እንደተደረገለት እና የተሻለ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በማራቶኑ ድጋፍ ለሰጡት ቤተሰቦቹ፣ጓደኞቹ፣ ለኢትዮጵያውያን እና ለአለምአቀፍ ደጋፊዎቹ ምስጋና አቅርቧል፡፡