አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዩክሬን ወታደሮች በሩሲያ ኩርስክ ግዛት አቋማቸውን እያጠናከሩና ድል እየተቀዳጁ መሆናቸውን የሀገሪቱ የጦር ኃይሎች አዛዥ ኦሌክሳንድር ሲርስኪ ተናገሩ፡፡
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ኪየቭ ከነሐሴ 6 ቀን 2024 ጀምሮ በአካባቢው 1 ሺህ 150 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው ሥፍራ 82 መንደሮችን መቆጣጠሯን አስታውቋል፡፡
ይህም ሩሲያ በዚህ ዓመት በዩክሬን ከተቆጣጠረችው ቦታ የበለጠ ነው ማለቱን ማላ ሜይል ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ በጦር አዛዡ ከቀረበላቸው ሪፖርት በኋላ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ዩክሬን አቋሟን እያጠናከረችና አካባቢዎችን እየተቆጣጠረች እንደምትገኝ ገልፀዋል፡፡
የኪየቭ ባለሥልጣናት ቢያንስ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሩሲያ ወታደሮች እንደታሰሩና በሩሲያ ከተያዙ የዩክሬን ተዋጊዎች ጋር በፍጥነት ለመለዋወጥ ተስፋ ማድረጋቸውን ዘገባው አመላክቷል፡፡
የዩክሬንን ጥቃት “ታላቅ ትንኮሳ” ያለችው ሩሲያ በበኩሏ ጎርዴቭካ እና ሩስኮ ፖሬችኖ አቅራቢያን ጨምሮ በበርካታ አካባቢዎች አጸፋዊ ምላሽ መስጠቷን ገልጻ÷ ይህንንም አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቃለች፡፡