አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ እንዲተገበር በትኩረት ይሰራል ሲሉ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ።
የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የ2017 ዓ.ም የመጀመሪያው እና ሁለተኛ ምዕራፍ ዕቅድ እየተገመገመ ነው፡፡
በመድረኩ ላይ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብረሃም በላይ (ዶ/ር)፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር)፣ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የግብርና ሚኒስትር ዴዔታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
አብርሃም (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በቆላማ አካባቢዎች ያለውን ፀጋ በመጠቀም የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በስምንት ክልሎች ተግባራዊ የሚደረገውን ሁለተኛ ዙር የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት በስኬት ለማጠናቀቅም በትብብር ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ፕሮጀክቱ በትክክል ተተግብሮ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርግ አስፈላጊው ድጋፍ እና ክትትል እንደሚደረግ ጠቁመው÷ ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ በማድረግ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ 424 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር መያዙንም አስታውቀዋል፡፡
በአሸናፊ ሽብሩና ብርሃን ደሳለኝ