ቴክ

በዲጂታል ግብይት ውስጥ ሊፈጸሙ የሚችሉ የፋይናንስ ማጭበርበር ድርጊቶች የትኞቹ ናቸው?

By Melaku Gedif

August 16, 2024

በዲጂታል ግብይት ውስጥ ሊፈጸሙ የሚችሉ የፋይናንስ ማጭበርበር ድርጊቶች የትኞቹ ናቸው?

1. ሀሰተኛ ሰነዶችን ማቅረብ፣

ከአበዳሪው ብድር ለማግኘት ሲባል ሀሰተኛ ሰነድ በማቅረብና በማጸደቅ አበዳሪዎችን ለማታለል የሚሞክርበት የማጭበርበር የወንጀል ድርጊት ነው።

2. የማንነት ስርቆት፣

ከአበዳሪው ብድር ለማግኘት ወይም ከፋይናንስ ተቋሙ አገልግሎት ለማግኘት የሌላ ሰውን ማንነት በመጠቀም የሚፈጸም ማጭበርበር ድርጊት ነው። ስለሆነም የደንበኛውን ትክክለኛ ማንነት በህጋዊ መታወቂያ፣ በስልክ ቁጥር እንዲሁም ሌሎች የደንበኛን ማንነት ለማወቅና ለማጣራት የሚያስችሉ ሂደቶችን በመጠቀም የማጭበርበር ወንጀል ድርጊት ሙከራዎችን ቁጥጥር ስር ማዋል ያስፈልጋል ማለት ነው።

3. የውሸት መረጃ፣

ይህ የፋይናንስ ማጭበርበር ድርጊት አንድ ሰው ስለገቢው ወይም ንብረቱ የውሸት መረጃ ማቅረብን የሚመለከት ነው። አንዳንድ የማጭበር ወንጀል ድርጊት ፈጻሚዎች እነሱን በሚመለከት ሀሰተኛ ዋቢዎችን ወይም ምስክርነቶችን ወይም ማጣቃሻዎችን በተባባሪዎያቻቸው አማካኝነት ሊያቀርቡ ይችላሉ።

4. የማስያዣ ዋስትና ማጭበርበር፣

ብድር ጠያቂዎች ብድር ለማግኘት እንደ ዋስትና የሚያቀርቡት ማስያዣ አስመልክቶ በሚያቀርቡት ማመልከቻ ላይ የውሸት መረጃ በማቅረብ የሚፈጸም የወንጀል ድርጊትን ይመለከታል። ይህ ደግሞ የንብረቱን ዋጋ እያወቁ ገቢን ከፍ በማድረግ ወይም በማጋነን በአበዳሪው የፋይናንስ ተቋም የብቁነት መስፈርት መሰረት ሊሰጥ ከሚገባው በላይ ብድር ማግኘትን ዓላማው ያደረገ ነው።

5. ፊሽንግ፣

ፊሽንግ በመባል የሚታወቀው የፋይናንስ ማጭበርበሪያ አይነቱ ትክክለኛ በሚመስል ማንነት ኢሜይሎችን፣ ድረ-ገጾችን ወይም የስልክ ጥሪዎችን በመጠቀም የሚፈጸም ሲሆን ዓላማውም ሚስጢራዊ መረጃ ለማግኘት የሚፈጸም ማጭበርበር ነው። እንዲህ አይነት ሁኔታዎች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ታሳቢ በማድረግ ብድር ለማግኘትና መሰል ጥያቄዎች የሚቀርቡ ሰነዶችን ምንም እንኳን ሲታዩ ትክክለኛ ቢመስሉም በአግባቡ መፈተሽና ትክክለኛነታቸውን ማረጋገጥ ተገቢ ጠቃሚ ይሆናል።

6. ካርድ ስኪሚንግ፣

የካርድ ስኪሚንግ ወንጀለኞች ከኤቲኤም ወይም ከዴቢት ካርድ የማግኔቲክ ማሰሪያ መረጃ የሚያገኙበት ነው። መረጃው የካርድ ባለቤቱን ስም፣ የካርድ ቁጥር እና የማብቂያ ቀንን ሊያካትት ይችላል። ይህም ሲባል በኤቲኤም ወይም በሽያጭ ነጥብ ተርሚናል ላይ የተያያዘ ትንሽ መሳሪያ መረጃውን በማንበብ ወደ አጭበርባሪው አካል ያስተላልፋል ማለት ነው። የማጭበርበር ድርጊት ፈጻሚውም መረጃውን በመጠቀም ያለባለቤቱ ፈቃድ ግዢዎችን ሊፈጽም ወይም ገንዘብ ሊያወጣ ይችላል ማለት ነው።

7. ሀሰተኛ የሂሳብ መግለጫዎች፣

ሀሰተኛ ሰነድ የፋይናንስ ተቋማትን በማታለል የታክስ ቅናሽ ለማግኘት ወይም በሕገ-ወጥ መንገድ የብድር ጥያቄ በማቅረብ ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚደረግ የማጭበርበር ስልት ነው።

ከዚህ አይነት የማጭበርበር ድርጊት ለመጠበቅ በየጊዜው የሂሳብ መግለጫዎችን መፈተሽ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ይመከራል። የትኛውም ልዩነት ሲያጋጥጥምም ወዲያውኑ አጠራጣሪውን የፋይናንስ እንቅስቃሴ ሪፖርት ማድረግ እንደሚያስፈልግ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡

በዲጂታል ግብይት ውስጥ በሚፈጸም የፋይናንስ ማጭበርበር ጉዳት የሚደረሰው የማጭበርበር ድርጊቱ ሰለባ የሆነ ግለሰብ ወይም ድርጅት ብቻ ሳይሆን ጉዳዩ የሚመለከተው የፋይናንስ ተቋም መልካም ስም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል። በተጨማሪም የሚጠቀሙባቸው አገልግሎቶችን ደህንነት በአግባቡ አለመጠበቅ አግባብ ባለው ህግ ተጠያቂ መደረጉም ሌላው ጉዳይ ነው።