አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በ2030 ኃይል ማመንጨት አቅምን በማጎልበት ሽፋኑን በአራት እጥፍ ለማሳደግ መንግሥት ግብ አስቀምጦ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዲሁም ከዓለም ዓቀፉ የንግድና ልማት ተቋም ጋር በመተባበር÷ የሀገሪቱን ኢነርጂ አቅርቦት በፋይናንስና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመደገፍና ለማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት ምክክር አካሂዷል፡፡
በዚሁ ወቅትም የኢነርጂ ኢንቨስትመንት ዘርፍ በኢትዮጵያ ቅድሚያ ትኩረት ከተሰጡት መካከል አንዱ መሆኑ ተገልጿል፡፡
መንግሥት በዘርፉ የግል ባለሃብቱን ተሳትፎ ይበልጥ ለማሳደግ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ እንደሚሰጥ መገለጹንም የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡
መንግሥት በ2030 የሀገሪቱን የኃይል ማመንጨት አቅም በማጎልበትና ሽፋኑን በአራት እጥፍ ለማሳደግ ግብ አስቀምጦ እየሠራ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
መድረኩ በዘርፉ ያሉ መልካም ዕድሎችን ከመጠቀምና የሚስተዋሉ ችግሮችን ከመፍታት አንጻር በቅንጅት መሥራት ላይ ያተኮረ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡