አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ለመጠባበቂያ እህል ክምችት የሚውል 43 ሺህ 581 ሄክታር መሬት በመኸርና በበጋ ወራት እርሻ በማልማት 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየሰራ መሆኑን ቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ ገለጸ።
በክልሉ ከማኅበረሰቡ የቆየ የመረዳዳት እሴት ተቀድቶ “ቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ” በሚል ስያሜ በተቋም ደረጃ ተቋቁሞና ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን እየሰራ ይገኛል።
የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ ኃላፊ ሞገስ ኢደኤ እንደገለጹት÷ እንደ ሀገር የተያዘውን አቅጣጫ መሠረት በማድረግ በክልሉ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ተደርጓል።
በዚህም ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመውጣት ሁሉም በየደረጃው መሥራት እንዳለበት መግባባት ላይ መደረሱን ገልፀዋል።
በክልሉ ሊከሰቱ ለሚችሉ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች፣ በዕድሜ ለገፉና ማምረት ለማይችሉ ዜጎች በራስ አቅም የሰብዓዊ ድጋፎችን ማቅረብ እንዲቻል ወደ ሥራ ተገብቷል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በዚህም በክልሉ ለመጠባበቂያና ለዕለት ደራሽ እህል ክምችት የሚውል 43 ሺህ 581 ሄክታር መሬት የማልማት ሥራ መጀመሩንም ጠቅሰዋል።