የሀገር ውስጥ ዜና

የአሸንዳ ዓይኒ ዋሪና ማሪያ በዓልን በድምቀት ለማክበር የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለፀ

By Feven Bishaw

August 16, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል የአሸንዳ ዓይኒ ዋሪና ማሪያ በዓልን በድምቀት ለማክበር የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለፀ።

በቢሮው የደረጃና ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክተር እና የበዓሉ ዝግጅት አስተባባሪ አቶ የማነ ገድሉ÷ በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር እንዲቻል ኮሚቴ ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራት ማከናወኑን አስረድተዋል።

በዝግጅት ምዕራፉ ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል የፀጥታና ጥበቃ፣ የመብራት፣ የውሃና የኢንተርኔት እንዲሁም የፅዳትና ውበት ተግባራት እንደሚገኙባቸው አመልክተዋል።

በዓሉን ለማክበር የሚመጡ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር እንግዶች የሚያርፉባቸው ሆቴሎችን ጨምሮ ሌሎች ደረጃቸውን የጠበቁ ከ175 በላይ ሆቴሎች ዝግጁ ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ባለፈው ዓመት የአሸንዳ ዓይኒ ዋሪ ማሪያ በዓልን ለማክበር ከ120 ሺህ በላይ ታዳሚዎች መገኘታቸውን አስታውሰዋል።

የዘንድሮው የአሸንዳ ዓይኒ ዋሪና ማሪያ በዓል ”የአሸንዳ ፀጋዎች ለአሸንዳ ልጃገረዶች ክብርና መፃኢ ብሩህ ዘመን” በሚል መሪ ሃሳብ ከነሐሴ 16 እስከ ነሐሴ 24 ቀን 2016 ዓ.ም በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት ይከበራል።