አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአንዳንድ የፖሊስ አመራርና አባላት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችንና የሥነ-ምግባር ግድፈቶችን በማረም አገልግሎት መስጠት ይጠበቅብናል ሲሉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ገለጹ፡፡
ፖሊስ መልካም ሥነ-ምግባር ተላብሶ ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥና አገልግሎቱን የበለጠ ለማዘመን በሚያስችል ሠነድ ላይ የፌደራል ፖሊስና የአዲስ አበበ ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች ውይይት አካሄዱ፡፡
በዚሁ ወቅት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል እንደገለጹት ÷ የኢትዮጵያን የፖሊስ አገልግሎት የበለጠ ለማዘመን በከፍተኛ ተነሳሽነት እየተሰራ ነው፡፡
በፖሊስ አገልግሎት ላይ ቅሬታ ያለው ማንኛውም ሰው በፌደራል ፖሊስ የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን በመጠቀም ቅሬታውን እንዲያቀርብም ፖሊስ የፌዴራል ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በተጨማሪም በአንዳንድ የፖሊስ አመራርና አባላት ላይ የሚስተዋሉ የሥነ-ምግባር ጉድለቶችን ለማረም በሚደረገው ከፍተኛ ጥረት ውስጥ ኅብረተሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ መቅረቡን ከፌደራል ፖሊስ የተገኘው መራጃ ያመላክታል፡፡
ከፍተኛ አመራሮቹ በፖሊስ ውስጥ የሚስተዋሉ አንዳንድ የሥነ-ምግባር ጉድለቶችና ብልሹ አሠራሮችን በፍጥነት በማረም ለኅብረተሰቡ ፈጣንና ፍትሃዊ አገልግሎት ለመስጠት ስምምነት ላይ ደርሰዋል ተብሏል፡፡