የሀገር ውስጥ ዜና

ለልማት ስራዎቻችን ስኬት የመከላከያ ሠራዊቱ ሚና ከፍተኛ ነው – አቶ ሙስጠፌ መሐመድ

By Meseret Awoke

August 15, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2016(ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል እየተከናወኑ ላሉ የልማት ስራዎች የመከለከያ ሠራዊቱ ሚና ከፍተኛ መሆኑን የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ገለፁ።

ለጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላና ለጄነራል መኮንኖች በጎዴ አየር ማረፊያ አቀባበል ያደረጉት ርዕሰ መስተዳድሩ ፥ የጎዴ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን ጨምሮ በከተማው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችንም አስጎብኝተዋል።

በክልሉ ያሉት የልማት ስራዎች ያለምንም የፀጥታ ስጋት እየተከናወኑ ያሉት የመከላከያ ሰራዊቱ በከፈለው መስዋዕትነት መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ከሦስት ዓመታት በፊት አልሸባብ ሰርጎ ለመግባት አድርጎት የነበረው ሙከራም በጀግናው የመከላከያ ሰራዊት የከሸፈ ነው ሲሉም አውስተዋል።

የሶማሌ ክልል ህዝብና የመከላከያ ሰራዊቱ የቤተሰብ ያህል ቅርርብ ያላቸው ከመሆኑ የተነሳ የተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች ሲያጋጥሙም ሰራዊቱ ፈጥኖ የሚደርስ መሆኑን መግለጻቸውን ከመከላከያ ሠራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።