የሀገር ውስጥ ዜና

የሐረሪ ክልል የምክክር ተሳታፊዎች አጀንዳዎቻቸውን በይፋ ለኮሚሽኑ አስረከቡ

By Tamrat Bishaw

August 15, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስተባባሪነት በሐረሪ ክልል ሲካሄድ የነበረው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ዛሬ ተጠናቅቋል፡፡

ከነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ በነበረው ውይይት ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ሃሳባቸው የተደመጠበት ነበር።

ተሳታፊዎች በስድስት ቡድን በመከፋፈል አጀንዳቸውን በማደራጀት በየቡድኑ ሆነው ያደራጁትን አጀንዳ ለጠቅላላው ጉባኤ አቅርበዋል።

በዛሬው ዕለትም የስድስቱ ቡድን ተወካዮች ሰላሳዎቹ አንድ ላይ በመሆን የክልሉን አጀንዳ አጠናቅረው ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አስረክበዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ተገኘወርቅ ጌጡ (ዶ/ር) ምክክሩ ጥሩ ግብዓት የተገኘበት ተቀምጦ ለመወያየት እድል የተሰጠበት የመወያየት ባህል የዳበረበት እንደነበር አንስተዋል።

እንደ ሀገር ለሚደረገው አጀንዳ የመለየት እና የማጠናቀር መርሐ -ግብርም ጥሩ ግብዓት የተገኘበት እንደነበር አንስተዋል።

ዛሬ የሐረሪ ክልል የምክክር ተሳታፊዎች ያስረከቧቸው አጀንዳዎች ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክር ቤት የሚቀርቡ ይሆናል፡፡

በፈቲያ አብደላ