አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አንድ የሩሲያ ፍርድ ቤት ክሴኒያ ካረሊና የተባለች የአሜሪካ እና የሩሲያ ዜግነት ያላት ሴት ዩክሬንን ለሚደግፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት 51 የአሜሪካ ዶላር በመለገሷ ምክንያት የ12 ዓመት እስራት ፈርዶባታል።
ግለሰቧ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብላ የተፈረደባት ባለፈው ሳምንት በዝግ ችሎት ጉዳዩዋ ፍርድ ቤት ቀርቦ ከታየ በኋላ መሆኑ ተመላክቷል።
ኑሮዋን በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ ግዛት አድርጋ የነበረችው ሴት÷ በፈረንጆቹ 2021 የአሜሪካ ዜግነት ማግኘቷ ተጠቅሷል።
ባለፈው ጥር ወር ከሞስኮ በስተ-ምሥራቅ 1 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የካተሪንበርግ ከተማ ለቤተሰብ ጥየቃ ባቀናችበት ወቅት ለእስር መዳረጓ ነው የተነገረው።
አቃቤ ህግ የ15 ዓመት እስራት እንዲበየንባት ጠይቆ የነበረ ቢሆንም÷ በየካተሪንበርግ የሚገኘው ፍርድ ቤት በከፍተኛ የክህደት ወንጀል ክስ 12 ዓመት እንድትታሰር ፍርድ መስጠቱን ቢቢሲ ዘግቧል።
ካሪሊና ለዩክሬን ወታደሮች የጦር መሣሪያ ለሚያቀርብ ድርጅት ገንዘብ በማሰባሰብ በሩሲያ የደህንነት አገልግሎት ተከሳ እንደነበር ተገልጿል።
የሩሲያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በአሜሪካ ሳለች ሩሲያ ዩክሬንን በወረረችበት በፈረንጆቹ የካቲት 22 ቀን 2022 51 ነጥብ 80 የአሜሪካ ዶላር አንድ ጊዜ ለግሳለች።
የገንዘብ ልውውጧንም የሩሲያ ፌዴራል የደህንነት አገልግሎት (ኤፍ ኤስ ቢ) በስልኳ አማካኝነት እንዳወቀ ታምኗል።