የሀገር ውስጥ ዜና

ከካሜሩን የመጡ የልኡካን ቡድን አባላት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የልምድ ልውውጥ አደረጉ

By Shambel Mihret

August 15, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከካሜሩን የአካባቢ ጥበቃና ግብርና ሚኒስቴር የተውጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የልምድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡

ልኡካን ቡድኑን ተቀብለው ያነጋገሩት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ማሙሻ ሀይሉ÷ ተቋሙ በውሃ ሀብት አስተዳደር፣ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን እንዲሁም በኢነርጂ ልማት ዘርፎች መደራጀቱን አንስተዋል፡፡

በሶስቱም ዘርፎች የሚከናወኑ ተግባራትንና ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ከየዘርፉ የተውጣጡ አመራሮችም ገለጻ አድርገዋል፡፡

የውሃ ሀብት አስተዳደርን በተመለከተ የውሃ ሀብት መረጃ አያያዝ፣ የውሃ አካላት ደህንነት ጥበቃና በውሃ አጠቃቀም ላይም ገለጻ ተደርጓል፡፡

እንዲሁም ከንጹህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አቅርቦት ጋር ተያይዞ እየተሰራ ባለው የከተሞች የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና በገጠር የውሃ ሽፋን ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

እንዲሁም በኢነርጂ ልማት ዙሪያ እና ከዋና መስመር ውጪ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተተገበረ በሚገኘው የሶላር ኢነርጂና የባዮ ማስ እና አጠቃቀምና አሰራር ላይ ልዑካኑ ግንዛቤ እንዲይዙ ተደርጓል።

ልኡካኑ በብሔራዊ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ሳኒቴሽንና ሀይጂን ፕሮግራም አተገባበርና በታዳሽ ሀይል ልማት ልምድ መቅሰማቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡