የሀገር ውስጥ ዜና

በሀሰተኛ ማንነት የወራሽነት ማረጋገጫ አቅርበው ከ28 ሚሊየን ብር በላይ ሊመዘብሩ ነበር የተባሉ ግለሰቦች ላይ ክስ ቀረበ

By Shambel Mihret

August 15, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀሰተኛ ማንነት የፍርድ ቤት የወራሽነት ማረጋገጫ አቅርበው ከግለሰብ የባንክ ሂሳብ 28 ሚሊየን ብር ሊመዘብሩ ነበር የተባሉ ግለሰቦች ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት ክስ ቀረበ፡፡

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ በሶስት ተከሳሾች ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ ቁጥር አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና የሙስና ወንጀሎች ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 32 ንዑስ ቁጥር 1፣ 2 እና 3 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ ክስ አቅርቦባቸዋል።

ተከሳሾቹ 1ኛ ዳዊት አይዳኙህም አጎናፍር፣ 2ኛ አስራኤል ወልዴ ድንቁ፣ 3ኛ የቅሊንጦ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ አባል የነበረ ኮንስታብል ሀብታሙ ተመስገን ናቸው።

ተከሳሾች ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለራሳቸው ለማግኘት በማሰብ ማንነታቸውን በመሰወር በተለይም 1ኛ ተከሳሽ ነዋሪነቱ በአዳማ ከተማ ሆኖ እያለ ማንነቱን በመቀየር አፋር ክልል ገቢረሱ ዞን በገለአሎ ወረዳ ገፍራም 2 ቀበሌ ነዋሪ ሳይሆን ነዋሪ ነኝ በማለት የሟች አድማሱ ምህረቱ ልጅም ሆነ ወራሽ ባልሆነበት ሁኔታ ወራሽ እንደሆነ በማስመሰል “አብነት አድማሱ ምህረቱ” ስም በተጭበረበረ መንገድ የነዋሪነት መታወቂያ ማውጣቱን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ አስፍሯል።

በዚህ መልኩ በተጭበረበረ ስምና መታወቂያ አፋር ክልል ገቢረሱ ዞን በገለአሎ ወረዳ ፍርድ ቤት በመጋቢት 5 ቀን 2016 ዓ.ም የአቶ አድማሱ ምህረቱ ወራሽ እንደሆነ በማስመሰል የፍርድ ቤት የወራሽነት ማረጋገጫ ማውጣቱ በክሱ ዝርዝር ላይ ተገልጿል፡፡

2ኛ ተከሳሽም የተከሳሽ “አብነት አድማሱ” ስም በተጨበረበረ መንገድ የወጣ መታወቂያ በመጠቀበም የፍርድ ቤት የወራሽነት ማረጋገጫ እንዲወጣለት በማድረግ 1ኛ እና 3ኛ ተከሳሾችን ከአዳማ ከተማ ወደ አዲስ አባባ ጉዞውን በማመቻቸት 3ኛ ተከሳሽ ፖሊሳዊ የደንብ ልብስ በመልብስ ከ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ጋር በመሆን መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ከሟች አድማሱ ምህረቱ 28 ሚሊየን ብር ለማውጣት ከ2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ጋር በአካል ቀርቦ እንደነበርና የባንኩን እምነት ለማግኘት እና ክፍያ እንዲፈፀምላቸው 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች የንግድ ባንክ ሰራተኞችን ለወራሽ ገንዘቡን አስተላልፉለት በማለት የንግድ ባንክ ደንበኛ ከነበሩት ከሟች አድማሱ ምህረቱ 28 ሚሊየን ብር ወደ 1ኛ ተከሳሽ ሂሳብ ሊያተላለፉ ሲሉ የተያዙ መሆናቸውን ተጠቅሷል፡፡

በዚህም በዋና ወንጀል አድራጊነት በህዝብ አስተዳደርና አገልግሎት ላይ በሚፈፀም ከባድ ማታለል የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

ተከሳሾቹ ዛሬ በተረኛ ችሎት ቀርበው ችሎቱ ማንነታቸውን በማረጋገጥ የክሱ ዝርዝር እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

ተከሳሾቹም የቀረበባቸው ክስ ላይ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ፍርድ ቤቱን የጠየቁ ሲሆን÷ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ ዋስትና በሚያስከለክል ድንጋጌ ስር መከሰሳቸውን ገልጾ ተከራክሯል።

ችሎቱ የግራ ቀኝ ክርክሩን መርምሮ የተከሳሾችን የተከሰሱበት ድንጋጌ ዋስትና በሚያስከለክል ድንጋጌ ስር መሆኑን ጠቅሶ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ትዕዛዝ በመስጠት ለጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡

በታሪክ አዱኛ