Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአመለካከትና የተግባር አንድነትን በማጎልበት የሐረሪ ክልልን የብልፅግና ጉዞ ለማስቀጠል ይሰራል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአመለካከትና የተግባር አንድነትን በማጎልበት የሐረሪ ክልልን የብልፅግና ጉዞ ለማስቀጠል ርብርብ ይደረጋል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ገለፁ።

በ2016 በጀት ዓመት ለውጥ አምጪ እሳቤዎችን በመላበስና በመተግበር የህዝቡን የአብሮነት እና የመረዳዳት እሴቶችን በማዳበር፣ ሰላምን በማስፈን እና ህዝቡን ለልማት ስራዎች በማስተባበር በሁሉም ዘርፎች አንፀባራቂ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልፀዋል።

ፓርቲውን በአስተሳሰብ ፣ በአደረጃጀት እና በተልዕኮ አፈፃፀም የማጠናከሩ ስራ ጥሩ መሻሻል ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ አመራሩ በቅንጅት በመረባረብ ህዝቡን በንቃት ማሳተፍ እና ጠንካራ የድጋፍና ክትትል ስራዎች መስራት ለስኬቱ ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።

በተጀመረው በጀት ዓመትም አባላትንና ህዝቡን በማሳተፍ የተጀመሩ አበረታች ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ ርብርብ እንደሚደረግ አመላክተዋል።

በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን በመቅረፍ እመርታዊ ውጤት እንዲመዘገብ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

ጠንካራ የፓርቲ ተቋም መፍጠር፣ የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲን እና የአሰራር ግልጽነትን ማስፈን እንዲሁም የክትትልና ቁጥጥር ስርዓት በማበጀት በኩል የተጀመሩ ተግባራት እንደሚጠናከሩም ጠቁመዋል።

Exit mobile version